Fana: At a Speed of Life!

8 የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዛወር የወጣው ጨረታ ለአንድ ወር ተራዘመ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 13 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ወደግል ለማዛወር ያወጣውን ጨረታ ለአንድ ወር ማራዘሙን አስታወቀ።

ባለፈው አመት መጨረሻ መንግስት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዛወር ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም ጨረታው እስከ ፈረንጆቹ ሕዳር 30 ቀን ድረስ ለባለሃብቶች ክፍት የነበረ ሲሆን፥ አሁን ላይ ጨረታው ለተጨማሪ አንድ ወር እስከ ፈረንጆቹ ታህሳስ 31 ቀን ድረስ መራዘሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጨረታው የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎም ጨረታው መራዘሙንም ነው የገለጸው።

መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጎ ወደ ስራ ገብቷል።

ከዚህ ውስጥም የግሉ ዘርፍ በስኳር ኢንዱስትሪው የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ በዘርፉ ማሻሻያዎች ማድረጉንም ነው ያስታወቀው።

ከዚህ አንጻርም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ባለሐብቶች የስኳር ፋብሪካዎችን ወደግሉ ዘርፍ ለማዛወር በወጣው ጨረታ እንዲሳተፉ ጥሪውን አቅርቧል።

ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3 ፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ የስኳር ፋብሪካዎች ለጨረታ ቀርበዋል።

ጨረታው ተወዳዳሪነትን እና የስኳር ምርታማነትን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ያለመ መሆኑንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል።

ይህም ኢትዮጵያ ለስኳር ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት፥ ገቢን ለማሳደግ ብሎም የሸንኮራ አገዳ አምራቾችን ሕይዎት ለማሻሻል እንደሚረዳም ታምኖበታል።

ከዚህ ባለፈም ጥሬ እና ያለቀለት የሸንኮራ አገዳ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚረዳም ነው የተመላከተው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.