የመከላከያ ሠራዊቱን የሚመጥን የመከላከያ አዋጅ ሊወጣ ይገባል- የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሠራዊቱን የሚመጥን ራሱን የቻለ የመከላከያ አዋጅ ሊወጣ ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
ዛሬ በተካሔደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ÷ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ለማሻሻል ራሱን የቻለ የመከላከያ አዋጅ ሊወጣ እንደሚገባ የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል፡፡
ለሀገር አለኝታ ለሆነው ለመከላከያ ሠራዊት ክብር የሚመጥን የደመወዝና የካሳ ክፍያ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በሚገባ እንዲከበሩ ራሱን ችሎ የመከላከያ አዋጅ ቢወጣ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ነው አባላቱ ያመላከቱት፡፡
የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተሥፋዬ በልጅጌ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ እንዲሻሻል በሰጡት ማብራሪያ÷ ከጡረታ መውጫ ዕድሜ ጣሪያ አወሳሰንና የጡረታ ዕድሜ ከማራዘም ጋር በተገናኘ፣ ከሠራዊት መብትና ጥቅማጥቅሞች አንጻር መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች በአዋጅ ማሻሻያው እንዲካተቱ ትኩረት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይም የሀገርን ኅልውናን አደጋ ላይ የሚጥል ጦርነት ሲከሰት የሠራዊት አባል የነበሩትን መልሶ ከመቅጠር ጋር በተገናኘ ስለሚኖረው አፈጻጸም፣ ስለ ብሔራዊ አገልግሎት፣ ሌሎች የአፈጻጸም ክፍተት ያለባቸውን ጉዳዮች ለማስተካከል የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስገንዝበዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጡረታ ከወጡ በኋላ ሠራዊቱን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲያገለግሉ ራሱን የቻለ የመከላከያ ሠራዊት ምክር ቤት ሊቋቋም እንደሚገባም ከምክር ቤት አባላት አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱን መብትና ግዴታዎች፣ የጡረታ መውጫ ጊዜና ጥቃማጥቅሞች እንዲከበሩለት አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ በአጽንኦት ሊመለከተው እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ የመከላከያን ረቂቅ አዋጅ ውሳኔ ቁጥር 9/2015 በማድረግ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!