በእሳት አደጋ የሁለት ሕጻናት ሕይወት ሲያልፍ በሦስተኛው ታዳጊ ላይ የአካል ጉዳት ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ የሁለት ሕጻናት ሕይወት ሲያልፍ በሌላ ታዳጊ ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት÷ ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጨፌ ሥላሴ አካባቢ በመኖሪያ ቤት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የሦስትና የአራት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት ሕጻናት ሕይወት አልፏል፡፡
በተጨማሪም በአንድ የሰባት ዓመት ታዳጊ ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ያልነበረውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመተካት የተለኮሰው ሻማ ለአደጋው መንስኤ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የሕጻናቱ እናት ለልጆቿ ደኅንነት በማሰብ የቤቱን በር ከውጭ ቆልፋ ወደ ሥራ መሔዷ ደግሞ የሕይወት አድኑን ሥራ ውስብስብ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ደኅንነት በማሰብ ልጆችን ከቤት ውስጥ አስቀምጠው በር መቆለፍን እንደ ብቸኛ መፍትሔ ከመውሰድ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን እንዲመለከቱ ኮሚሽኑ መክሯል፡፡
ከሻማ አጠቃቀም ጋር በተያያዘም ህብረተሰቡ አገልግሎቱን ካገኘ በኋላ የሻማውን መጥፋት በማረጋገጥ ከሚያደርሰው አደጋ እራሱን እንዲጠብቅ ተጠይቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!