Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየውን መደበኛ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየውን መደበኛ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ተናገሩ።
አየር መንገዱ ለዳግም በረራ መዘጋጀቱ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገልጿል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ በአየር መንገዱ ስኬትና ቀጣይ እቅዶች እንዲሁም የተቋሙን አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በማብራሪያቸው “በመንግስትና ህወሃት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየውን መደበኛ በረራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አስቀድሞ ወደ አካባቢው በየቀኑ በርካታ በረራዎች እንደነበሩ አስታውሰው ከክስተቱ በኋላ ግን አገልግሎቱ መቋረጡን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ የአገር ውስጥ በረራ ከሚያደርግባቸው በርካታ መዳረሻዎች መካከል የትግራይ ክልል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ዳግም በረራ ለመጀመር መዘጋጀቱ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
በመንግስትና በህወሃት መካከል የተደረገው ሰላም ስምምነት አየር መንገዱ ሲሰጣቸው የነበሩ መደበኛ አገልግሎቶችን ከመስጠት ባለፈ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትን ለማፋጠን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
በክልሉ ከሚገኙ ኤርፖርቶች መካከል የመቀሌ እና የሽሬ አየር ማረፊያ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ለበረራ ምቹ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአክሱም ኤርፖርት ግን በግጭቱ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ ለበረራ በሚመች መልኩ ማስተካከያ የሚጠይቅ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ መዳረሻዎች ዳግም በረራ ለመጀመር መዘጋጀቱ በክልሉ በተለይም ሰብዓዊ ድጋፍን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይም የአፍሪካ አህጉርን በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ሰፊ ራዕይ ሰንቆ በመስራት ላይ መሆኑ ይታወቃል።
አየር መንገዱ አሁን ላይ ያሉትን 207 አጠቃላይ መዳረሻዎች እኤአ በ2035 ወደ 271 ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.