Fana: At a Speed of Life!

እየተገነባ ያለው የባህር ኃይል አቅም ለነገው ትውልድ መሰረት የሚጥል ነው – ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተገነባ ያለው የባህር ኃይል አቅም ለነገው ትውልድ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ፡፡

ዋና አዛዡ በቢሾፍቱ መከላከያ ኢንጅነሪግ ግቢ ባቦጋያና በመከላከያ ኢንጅነሪግ ኮሌጅ ለሙያዊ ስልጠና ለመግባት ለተዘጋጁ መሰረታዊ የባህር ኃይል ሙያተኞች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የመሰረታዊ ባህርኞችን አቅም በእውቀት ለመገንባት የሚያስችሉ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል፡፡

ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ባህረኞች የሚሰጣቸውን ሙያዊ ስልጠና ትኩረት ሰጥተው መማር እንዳለባቸው ጠቁመው÷እየተሰጠ ያለው ስልጠና ቡድናዊ እና ተናጠላዊ ተልዕኮን በውጤት ለመወጣት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባህር ኃይልን አቅም በመገንባት ለነገው ትውልድ መሰረት የመጣል ስራ ይሰራል ያሉት ሬር አድሚራል ክንዱ÷ በአሁኑ ወቅትም የባህር ኃይል ማሰልጠኛ ትምህርት ቤትን መሰረተ ልማት ለማሟላት የግንባታ ስራዎች በተለይ የመሰረታዊ ባህርኛ ማሰልጠኛ ት/ቤት ግንባታ መጀመሩን አንስተዋል፡፡

ሌፍተናንት ኮማንደር ትዕዛዙ አለምነህ በበኩላቸው ÷ ባህር ዳር የነበሩ መሰረታዊ ባህረኞች አንድን ባህረኛ ብቁ ሊያደርግ የሚችለውን ትምህርትና ስልጠና ሲከታተሉ ቆይተው ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይም ወደ ዋናው የሙያ ላይ ስልጠና ለመግባት የተዘጋጁ እንደሆነ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.