Fana: At a Speed of Life!

የአየር ንብረት ለውጥ ለአፍሪካ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለችግሩ መፍትሔ ማፈላለግ ያስፈልጋል – አቶ ዑመር ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ ለአፍሪካ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለችግሩ መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚያስፈልግ የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን ገለጹ፡፡
 
ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ያለው የግብርና የ15 ዓመት የኢንሹራንስ ልምድ እና ዓለም አቀፍ የግብርና ኢንሹራንስ ተሞክሮዎችን የሚያስቃኙ ሰነዶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
 
የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን በመድረኩ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር÷ አፍሪካ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ፣ በጎርፍ እና በድርቅ በመጎዳቷ ገፅታዋ እየተቀየረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ ለአፍሪካ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ የችግሩን አያያዝ መንገዶችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
 
ለዚህም አንዱ አፋጣኝ እርምጃ የግብርና ኢንሹራንስ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የጠቆሙት፡፡
 
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው÷ መድረኩ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የግብርና ኢንሹራንስ ላይ ያሉ ጠንካራ ጎኖች፣ ተግዳሮቶች እና በቀጣይ እንዴት እንስራ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ከመድረኩ ተሳታፊዎች የግብርና ኢንሹራንስን የተመለከቱ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ወይይት ተደርጎባቸው የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.