Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ጋር ዛሬ በኒጀር ኒያሚ ተወያይተዋል።
በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ”የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማት ለአካታችና ዘላቂ የኢንዲስትሪ ዕድገትና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ማስፋት” በሚል ርዕስ ኒጀር መዲና ኒያሚ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ስብሰባ እየተሳተፈ ነው።
ከስብሰባው ጎን ለጎን አቶ ደመቀ ከሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር ባደረጉት ውይይት በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሐት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት የአፍሪካ ሕብረት ሚና ወሳኝ እንደነበር ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እና በኋላ ላይም በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ በተደረጉ ስምምነቶች የአፍሪካ ሕብረት ላሳየው በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም አቶ ደመቀ ምስጋና አቅርበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ቁርጠኛ እንደሆነ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ኢንሼቲቭ ላይ ያሳየውን የፀና እምነት አድንቀዋል።
ሊቀመንበሩ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.