በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እየሰሩ መሆኑን የደቡብ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እየሰሩ መሆኑን የደቡብ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አስታወቁ።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ የሃብት ማሰባሰብ ስራዎች ጀምረናል ብለዋል።
ለዚሁ ስራም በክልሉ ግብረ ሃይል መቋቋሙን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በዚህም እስካሁን 52 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
የአይነት ድጋፎችንም በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ርስቱ የተናገሩት።
እንዲሁም በጦርነቱ ለተለያዩ ስነ-ልቦናዊ እና ተያያዥ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖች የሚያስፈልጋቸውን ሙያዊ እገዛ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን በሁሉም ዘርፍ መልሶ የማቋቋም ስራ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሮቹ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ከማቅረብ ረገድ የሚያከናውኑትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን