Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግርን መቅረፍና ሌብነትን መከላከል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ለሚስተዋለው የፀጥታ ችግር መፍትሄ ማበጀትና ሌብነትን መከላከል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ገለፀ፡፡

ህዝብን ለምሬት የዳረጉ ችግሮች ተለይተው አቅጣጫ መቀመጡንና ወደ ስራ መገባቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

በክልሉ መንግስታዊ አገልግሎትን ለማግኘት እጅ መንሻ እንጠየቃለን የሚል ቅሬታ እንዳለ አንስተው ይህን ችግር የክልሉ መንግስት እንደሚያውቀውና የመለየት ስራዎችም ቀድመው ሲከናወኑ እንደቆዩ አስረድተዋል።

በዚህም በክልሉ ባለፈው አመት በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር የፈፀሙ 28 ሺህ ሰራተኞችና ሃላፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውሰው አጥፊን በመለየት የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሀን ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ጥፋተኞችን እንዲያጋልጡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ያሉት አቶ አወሉ የምርመራ ዘገባዎች ደግሞ ወንጀለኞችን እንዲያጋልጡ ይጠበቃል ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን ብሎም በቴክኖሎጂ ማገዝና ማደራጀትም ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ የተቀመጠ ስልት መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ክልሉን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ የሚሞክሩ ሀይሎች መዳረሻቸው ህዝብን ማህበራዊ እረፍት መንሳት መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህ ሀይሎች የሚያደርሱትን ጥቃት ለመመከት የሚወሰዱ እርምጃዎች ፍሬ ማፍራታቸውንም ነው የገለጹት።

የሚወሰዱ እርምጃዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አወሉ አብዲ ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን በመቆም በሌብነትና ህገወጦች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.