Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል – የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በክልሉ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በመንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ያለ ገደብ እየቀረበ ይገኛል፡፡

በሚኒስቴሩ የአስቸኳይ ጊዜ መጠጥ ውሃና ልዩ ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ አቶ አስቻለው ተስፋዬ፥ በሽረ ከተማ በሰከንድ 48 ሊትር የተጣራ ውሃ መልቀቅ የሚችል የውሃ ማጣሪያ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የመጠገን ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ከሽራሮ እስከ አድዋ ባሉ አካባቢዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም ተጨማሪ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በመጠለያ ጣቢያዎች ከድጋፍ ሰጪ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ውሃ በቦቴ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በዚህም በመጠለያ ጣቢያዎች የነበረውን የውሀ እጥረት መፍታት ተችሏል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.