Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 1ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በቦንጋ ከተማ ተከበረ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 11ኛ የፌዴሬሽኑ አባል በመሆን የተመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንደኛ አመት የምስረታ በዓል በቦንጋ ከተማ ተከበረ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በክልሉ በሚገኙ ህዝቦች መካከል አንድነት፣ እኩልነትና ፍትህን በማስቀደም ለክልሉ ልማት በቆራጥነት ልትሰሩ ይገባል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን እምቅ ሃብት ወደ ህዝባዊ ተጠቃሚነት ለመቀየር በትጋት ልትሰሩና ብልፅግናን ልታረጋግጡ ይገባልም ብለዋል ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው፥ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በክልሉ የተሞከረው የበጋ መስኖ ስንዴ ውጤት ማሳየቱንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የተገኘበት 64 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ መላክ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ ሰላምን ለማስፈን ዘርፈ ብዙ የሰላምና ፀጥታ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማልማት በሚደረገው ጥረትም ክልሉ ከኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቹ ጎን እንደሚቆም ቃል ገብተዋል።

የመሰረተ ልማት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ተጨማሪ የክልሉ ፈተና መሆናቸውን የፌደራል መንግስቱ እንዲያውቀው እንዲሁም ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ አይቶ ለመፍትሄው ከክልሉ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

በተለያዩ ሁነቶች በተከበረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንደኛ አመት የምስረታ በዓል ላይ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች መገኘታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.