አቢሲኒያ ባንክ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተጣራ እና 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የአቢሲንያ ባንክ የባለአክሲዮኖች 26ኛ ዓመታዊ መደበኛ እና 13ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ መኮንን ማንያዘዋል በዚህ ወቅት እንደተናገሩ ÷ ባንኩ ካለፈው በጀት ዓመት አንጻር ሲታይ የ127 በመቶ ጭማሪ ዕድገት ያለው ትርፍ አግኝቷል፡፡
ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የ 43 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ማስመዘገቡን የገለጹት ሊቀ መንበሩ ÷የባንኩ የሂሳብ ዓመት አጠቃላይ ካፒታልም ወደ 14 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ከፍ ብሏል ብለዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክም ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ተፅዕኖዎችን በመቋቋም በተቀማጭ ገንዘብ ፣ በአጠቃላይ ገቢ፣ በብድር፣ ቅርንጫፍ በማስፋፋትና በደንበኞች ቁጥር ጭማሪ አበረታች የሆኑ ውጤቶችን ማስመዝገቡም ተመላክቷል።
በትዕግስት አስማማው