Fana: At a Speed of Life!

ተጠባቂው የስፔን እና ጀርመን ጨዋታ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ምሽት ስፔን ከጀርመን የሚያደርጉት የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

በምድብ አምስት የተደለደሉት ሁለቱ ሀገራት ከምድብ ለማለፍ ምሽት 4 ሰዓት በኳታሩ አል ባይት ስታዲየም ፍልሚያቸውን ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

ኮስታሪካን በሰፊ ውጤት ያሸነፈችው ስፔን በጊዜ ከምድቡ ለማለፍ ጨዋታዋን የምታደርግ ሲሆን÷ ጀርመን በአንፃሩ በጃፓን የደረሰባትን ሽንፈት በመቀልበስ ከምድቡ ለማለፍ የምትጫወት ይሆናል፡፡

ስፔን የ2010 የዓለም ዋንጫን ካሸነፈች በኋላ በትልቁ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ውጤት ርቋት የቆየች ሲሆን÷ በ 2014ቱ የብራዚል የዓለም ዋንጫ ከምድብ ስትሰናበት በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ከምርጥ 16 ውስጥ ተሰናብታለች፡፡

የ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮናዋ ጀርመን በዓለም ዋንጫው የሻምፒዮናነት ግምት ቢሰጣትም በጃፓን ሳይጠበቅ 2 ለ 1 ተሸንፋለች፡፡

የስፔኑ አሰልጣኝ ሊዊስ ኤንሪኬ ኮስታሪካን ያሸነፉበትን ስብስብ ይዘው ወደ ሜዳ ይገባሉ የተባለ ሲሆን ÷ፌራን ቶሬስ፣ማርኮ አሴንሲዮ እና ዳኒ ኦልሞ የፊት መስመሩን ይመሩታል፡፡

ፔድሪ እና ሰርጂዮ ቦስኬት የመሀል ክፍሉን ሲመሩ አዝፕሊኬታ፣ላፖርት ፣አልባ እና ሮድሪ ደግሞ የተከላካይ ክፍሉን እንደሚመሩ ይጠበቃል፡፡

የጀርመኑ አሰልጣኝ ሃንሲ ፍሊክስ በበኩላቸው ÷ሰርጌይ ጊናብሪ፣ቶማስ ሙለር እና ጀማል ሙሴይላን በአጥቂነት እንዲሁም ጆሺዋ ኪሚቸ እና ኤልካይ ጎንዶጋንን በመሀል ክፍል ላይ እንደሚያሰልፉ ይጠበቃል፡፡
ኒኮላስ ሱሌ፣አንቶኒዮ ሩዲገር፣ኒኮ ሾልተርቤክ እና ዴቪድ ራውም ደግሞ የተከላካይ ክፍሉን ይመራሉ ተብሎ እደሚጠበቅ ስፖርት ስታር ዘግቧል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.