Fana: At a Speed of Life!

የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለው አመራር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቲቢ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲሁም አስፈላጊውን የሀገር ውስጥ ፋይናንስ ለማሳደግ በየደረጃው ያለው አመራር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አስገነዘበ፡፡

በአፍሪካ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና የተሻሻለ የሀገር ውስጥ ፋይናንስ ማሳደግ ላይ ያተኮረ አህጉራዊ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ÷ መንግስታት የቲቢ በሽታ ትልቅ የህዝብ የጤና ተግዳሮት መሆኑን እንዲገነዘቡና የቲቢ በሽታን ለማጥፋት በከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ደረጃ ጠንካራ አመራር መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም የውስጥ ፋይናንሳቸውን ለማሳደግ ውጤታማ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዎችን በማዘጋጀትና የቲቢ ስጋትን የሚጨምሩ አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ጉዳዮችን ለመፍታት እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በመድረኩ በተለያዩ ሀገራት የተወሰዱ ምርጥ ተሞክሮዎች፣ ዓለም ዓቀፍ እና ሀገራዊ ስትራቴጂዎች፣ ሁሉንም የቲቢ ዓይነቶችን ለመመርመር እና በተሳካ ሁኔታ ለማከም የተቀመጡ የቲቢ መከላከል እና ህክምና ግቦችን ለማሳካት የተረጋገጡ ዘዴዎችን አጠቃቀም ለማሳወቅ በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም ለተመራማሪዎች፣ አገልግሎቶችን ለማሻሻል እና ለመከታተል የሚረዱ ፖሊሲዎችን ለማሳወቅ የሚያስፈልጉ ሳይንሳዊ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ በአፍሪካ የብሔራዊ ቲቢ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጆች፣ የአካባቢ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ አጋሮች፣ የሲቪል ማህበራት፣ በቲቢ የተጠቁ ማህበረሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.