የሀገር ውስጥ ዜና

ለትግራይ ክልል ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

By Alemayehu Geremew

November 28, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሆን ከ10.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዛሬው ዕለት ሰብዓዊ ድጋፉን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ጉዞ የጀመሩ ሲሆን÷ በዚህም 1 ሺህ 500 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ 6 ሺህ ሊትር ዘይት፣ 150 ኩንታል ባቄላ ወደ ስፍራው በመጓጓዝ ላይ ይገኛል።

ድጋፉ ከዴንማርክ ቀይ መስቀል በተገኘ ገንዘብ በሁለት ዙር የተደረገ ሲሆን÷ ለተለያዩ ችግሮች ለተጋለጡ የትግራይ ክልል አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

ማህበሩ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ጉዳት ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡

ለትግራይ ክልልም የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ርብርብ የሚያደርግ ይሆናል ነው የተባለው።