Fana: At a Speed of Life!

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊታችን ሕዳር 29 በሀዋሳ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በድምቀት ለማክበር የሚያስችለውን መሰናዶ ማጠናቀቁን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ።

የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፈሰር ጸጋዬ ቱኬ በሰጡት መግለጫ÷ የከተማ አስተዳደሩና ሕዝቡ ለበዓሉ በድምቀት መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥተው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት የሚካሄድ መሆኑን በመግለፅ÷ እለቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት የተረጋገጠበት ቀን በመሆኑ በዓሉ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ነው ያሉት።

በመሆኑም የሁሉም ክልል ሕዝቦች የሠላምና የልማት መሠረት የሆነውን በዓል በድምቀት ለማክበር ሀዋሳ አስፈላጊ መሰናዶዎችን አጠናቃ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅታለች ብለዋል።

ከተማዋ ትልቅ ቦታና ትርጉም የሚሰጠውን በዓል ለማሰናዳት እድል በማግኘቷ ከንቲባው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ምስጋና አቅርበዋል።

በዓሉ በከተማዋ መከበር ትልቅ እድል ይዞ ይመጣል ያሉት ከንቲባው በተለይም ለመላው ኢትዮጵያውያን ሀዋሳ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለኮንፍረንስና ለኑሮ አመቺ መሆኗን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ታላቅ መድረክ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች እና የስራ አመራሮች በተገኙበት የሚከበረውን ታላቅ በዓል በሰላም ለማክበር በፀጥታው ረገድም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በንግዱ ማህበረሰብም የዋጋ ቅናሽ ከማድረግ ጀምሮ ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸው ያማረ እንዲሆን በተሻለ መስተንግዶ ለመቀበል ተሰናድተናል ብለዋል።

የከተማዋ ወጣት አደረጃጀቶችና የሰላም አምባሳደሮች እንዲሁም ነዋሪዎች ሀዋሳ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት ከተማ መሆኗን በሚያሳይ መልኩ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶቿንና የተለያዩ ብሔር ብሄሔረሰቦችን በአክብሮት፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በቆየ አብሮ የመኖር እሴትን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲቀበሉም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

በአከባበር ሂደቱም በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በቀጥታ በበዓሉ ላይ በመሳተፍ ባህላዊ ጭፈራዎችን አልባሳቶችንና የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ለእይታ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየሞች፣ ዐውደ ርዕዮች፣ ባህላዊ ትርኢቶች እና የባህል ልውውጦች በክብረ በዓሉ ላይ እንደሚካተቱም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.