Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ከ45 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ መሰራጨቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ከ45 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም 839 ሜትሪክ ቶን በላይ መድሃኒት መሰራጨቱን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
 
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በክልሉ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚከናወነውያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
 
በዚህ መሰረትም እስከ ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም በክልሉ በ1 ሺህ 17 ተሽከርካሪዎች 40 ሺህ 63 ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ ምግብ እና አልሚ ምግብ መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
 
በተጨማሪም በ25 ተሽከርካሪዎች 839 ነጥብ 76 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት እና በ115 ተሽከርካሪዎች ከ4 ሺህ 254 በላይ ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች ለተጎጂዎች መሰራጨታቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም 413 ሺህ 552 ሊትር ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ አካባቢው መላካቸውን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
 
ከጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሶስቱ ኮሪደሮች ( በአፋር አብአላ ፣ በጎንደር ሽረ እና በኮምቦልቻ ቆቦ አላማጣ) በአጋር አካላት የተሠማሩ ከባድ ተሸከርካሪዎች ብዛት 1 ሺህ 168 መሆኑን አንስተዋል፡፡፡
 
በክልሉ ለተሰማሩ 16 አጋር አካላት ለሚያከናውኑት የሰብዓዊ አቅርቦት ስራ ማስኬጃ 148 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም አቶ ደበበ ጠቁመዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.