ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ከማስወንጨፏ በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ሥርዓት ልትዘረጋ ነው

By Alemayehu Geremew

November 30, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎች ከመወንጨፋቸው በፊት ቅድመ-ማስጠንቀቂያ መሥጠት የሚችል ሥርዓት ልትዘረጋ መሆኑን አሜሪካ አስታወቀች፡፡

በትናንትናው ዕለት መቀመጫውን በዋሺንግተን ያደረገው ሚቼል የተሠኘው የአሜሪካ የዓየር እና የጠፈር ምርምር ተቋም በዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የበይነ መረብ ውይይት አካሂዷል፡፡

በተካሄደው ውይይትም አዲስ የተቋቋመው የአሜሪካ የጠፈር ኃይል ዕዝ ኃላፊ ጀነራል ጀምስ ዲኪንሰን ተሳትፈውበታል፡፡

ጀነራል ጀምስ ዲኪንሰን በሕንድ-ፓሲፊክ ቀጣና ከሰሜን ኮሪያ ማንኛውም ዓይነት ሚሳኤል የማስወንጨፍ ሙከራ ከተቃጣ አነፍንፎ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሥጠት የሚችል አሰራር ጀምረናል ብለዋል፡፡

የአገልግሎቱን ዕቅዶችም በዝርዝር ማቅረባቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ ዕቅድ አሜሪካን የመምታት ዐቅም ያለው ሚሳኤል ባለቤት ከሆነችው ሰሜን ኮሪያ ራሷን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን የሚሳኤል ሽታ አነፍንፋ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ለቀጣናው አጋሮቿ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ መሥጠት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡