ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቱርክ ከሶሪያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ እየከረረ በመጣው ወታደራዊ ፍጥጫ ዙሪያ ከኢራን ጋር መከረች

By Alemayehu Geremew

November 30, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር አብዶላሂያን እና የቱርክ አቻቸው ሜቭሉት ካቩሶግሉ በቱርክ እና በሶሪያ ድንበር እየተባባሰ ባለው ወታደራዊ ውጥረት ላይ መምከራቸው ተሰማ፡፡

ሚኒስትሮቹ በስልክ በነበራቸው ውይይት በሀገራቱ መካከል ቀጣይነት ያለው የፀጥታና የደኅንነት ውይይት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ጉዳዩን በወታደራዊ አማራጭ ለመፍታት ማሰብ ኪሳራ እንደሚያስከትልም በውይይታቸው አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ሁኔታውን የበለጠ እንደሚያወሳስበው የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር አብዶላሂያን ገልጸዋል፡፡

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው የኢራንን አወንታዊ ዲፕሎማሲ ያደነቁ ሲሆን መሠል ምክክሮች መቀጠል አለባቸው ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።

ቱርክ የኩርድ አማፂያንን ዒላማ ያደረጉ በሰሜን ኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ 500 የሚጠጉ ዒላማዎችን በዓየር ጥቃት መትቻለሁ ፤ አሸባሪዎችንም ደምስሻለሁ ማለቷ ይታወሳል፡፡