የሀገር ውስጥ ዜና

ሩሲያ በመረጃ መረብ ደኅንነት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገለፀች

By Feven Bishaw

December 01, 2022

አዲስ አበበ፣ ሕዳር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዲጂታላይዜሽን፣ በመረጃ መረብ ደኅንነትና በዲጂታል ክህሎት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትፈልግ ገለፀች።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ከሩሲያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ ምክትል ሚኒስትር ማክሲም ፓርሺን ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ዶክተር በለጠ ሞላ ሩሲያ ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይም በዲጂታል ክህሎት እና የመረጃ መረብ ደኅንነት ላይ ሩሲያ ያላትን ልምድ ኢትዮጵያ መካፈል ትልጋለች ብለዋል፡፡

ማክሲም ፓርሺን በበኩላቸው÷ በኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎት፣ በዲጂታል ክህሎት፣ በመረጃ መረብ ደኅንነት እና በሌሎችም ዘርፎች በትብብር እንሠራለን ማለታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡