Fana: At a Speed of Life!

ከሱዳን ግዛት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ አካላትን ሱዳን አትታገስም – ጀኔራል አልቡርሀን

አዲስ አበበ፣ ሕዳር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሱዳን ግዛት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ አካላትን ካርቱም አትታገስም ሲሉ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር በካርቱም ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሀገራቱ የሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ምክክር ማድረጋቸውን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትብብር እንዲጎለብት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀራርበው ለመስራት መስማማታቸውን ከሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን፥ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሐት መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ መደሰታቸውን ገልፀው፥ ሀገራቸው ለስምምነቱ አፈፃፀም ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት የሚያደናቅፉ እንደዚሁም ከሱዳን ግዛት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ አካላትን ሱዳን እንደማትታገስም አረጋገግጠዋል።

ከድንበር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ ዘላቂ መፍትሄን የማያመጣ በመሆኑ ቀደም ሲል ሁለቱ ሀገሮች በፈረሟቸው ስምምነቶች አማካኝነት በሁለትዮሽ መስመር ለመፍታት ከመግባባት መደረሱ ተመላክቷል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል እየታየ ያለ በጎ የትብብር መንፈስ ልዩነቱን በሦስትዮሽ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት አዎንታዊ አሰተዋጽኦ እንዳለውም እምነታቸውን ገልፀዋል።

ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና አቶ ደመቀ በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ህገወጥ የሰዎች፣ የጦር መሳሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በጋራ ለመከላከል ተስማምተዋል።

አቶ ደመቀ ቀደም ብለው ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጀኔራል መሀመድ ሀምዳን ደግሎ እና ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ አል-ሳዲቅ ጋርም ተወያይተዋል።

በዚህም ወቅት አቶ ደመቀ በሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በሱዳን ርዕሰመዲና ካርቱም በተካሄደው የኢጋድ የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ መሳተፋቸው ይታወቃል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ሱዳን መደሰቷን ገልፀው÷ ተግባራዊየቱን ሀገራቸው እንደምትደግፍና አዎንታዊ ሚና እንደምትጫወት አስታውቀዋል።

ሰላም ከሌለ ልማት የማይታሰብ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሰላም የሱዳን ሰላም እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በካርቱም የተካሄደው የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ እንዲሳካ ኢትዮጵያ ለዳረገችው አስተዋጽኦ እና ላሳየችው አጋርነት አመስግነዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.