Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ጉባዔን ልታስተናግድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የፌደራል ፖሊስ ገልጿል።

ለ24ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የፖሊስ አዛዦቹ ጉባዔ ከህዳር 25 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ነው በአዲስ አበባ የሚካሄደው።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ኢንተር ፖል መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ፀጋዬ ሃይሌ በየአመቱ የሚካሄደው ጉባዔ አላማው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች በየአመቱ እየተገናኙ የስራ አፈጻጸማቸውን የሚገመግሙበት ነው ብለዋል።

ጉባዔው በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ተለይተው የተቀመጡ ወንጀሎች፣ ሽብርተኝነት፣ ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ አደንዛዥ እፅ ፣የከብቶች ስርቆት እና ሌሎች የተለዩ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እና የጋራ የወንጀል መከላከል መለኪያ እንዲኖር አጋዥ እንደሆነ ኮማንደር ጸጋዬ ገልጸዋል።

በስብሰባው ቀደም ሲል ተግባራዊ የሆኑ መልካም ተሞክሮዎች እና ስራዎች ይገመገማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የህብረቱ ጉባኤ ቀጠናውን ከወንጀል ስጋት የጸዳ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

14 የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት አባል የሆኑበት የፖሊስ አዛዦች ህብረት በኢትዮጵያ መካሄዱ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ያላት መሆኑን እና ትላልቅ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ተመራጭ መሆኗን ማሳያ ነውም ተብሏል።

የቀጣይ የህብረቱን መሪነት የኢፌድሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል እንደሚረከቡም ተገልጿል።

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.