የሀገር ውስጥ ዜና

ጥምረት ለዲጂታል አፍሪካ የተሰኘ ኢንሼቲቭ ተመሰረተ

By Tamrat Bishaw

December 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 17ተኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ አይኬን (ICANN) የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጥምረት ለዲጂታል አፍሪካ የተሰኘ ኢንሼቲቭ አስጀምሯል።

ይፋ የሆነው ኢንሼቲቭ ለዲጂታል አፍሪካ ተመሳሳይ ዓላማና ሐሳብ ያላቸውን ተቋማት በአንድ ማሰባሰብና ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢንተርኔት መሰረተልማት ለአፋሪካውያንን ለመዘርጋት ያለመ ነው።

የአይኬን ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጎራን ማርቢ እንደገለጹት÷ የዲጂታል አፍሪካ ጥምረቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በትብብር ለመሥራት አዲስ ዕድል ይፈጥራል፡፡

ጥምረቱ አፍሪካን በኢንተርኔት መሰረተ ልማት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማስፋት፣ የኢንተርኔት ደኅንነትን ማረጋገጥ እና አፍሪካውያን የኢተርኔት አገልግሎትን በቋንቋቸው እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለዚህ አጋዥ የሆነው “የዶሜን ኔም ሲስተም” መሰረተ ልማትን ማስተናገድ እንዲቻልም በአይኬን የሚተዳደር ዋና የመረጃ ቋት ወይም ሩት ሰርቨር ክላስተር ባሳለፍነው ወር በኬንያ በይፋ ሥራ መጀመሩ ተነግራል፡፡

የአፍሪካ ቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት ዋና ጸሐፊ ጆን ኦሞ የቅንጅቱ መጀመር የኢንተርኔት መሠረተ ልማትን ለማጠናከር አንድ እርምጃ እንድንቀራረብ ያደርገናል ብለዋል፡፡

ጥምረቱ በአፍሪካ እየተዘረጉ ላሉ አሁናዊ የኦንላየን አገልግሎቶች መተማመን እንዲኖረን አቅም ይሆነናል ነው ያሉት፡፡

በፀጋዬ ወንድወሰን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!