የሀገር ውስጥ ዜና

በቀጣዮቹ 10 ቀናት በደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅዝቃዜው ሊጠናከር ይችላል- ኢንስቲትዩቱ

By ዮሐንስ ደርበው

December 02, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት በሰሜን ምሥራቅ፣ መካከለኛው እና የደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አመላከተ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከሕዳር 22 እስከ ታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አዝማሚያ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚሁ መሰረት በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የበጋው ደረቃማ፣ ፀሐያማውና ነፋሻማው የአየር ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖረው አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሌሊቱ እና የማለዳው ቅዝቃዜ ሊጠናከር እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

በመጨረሻዎቹ ቀናት ከሚጥናከረው የእርጥበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ÷ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በሶማሌ ክልል የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ዞኖች፣ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦር፣ አርሲ እና ባሌ፣ ከጋምቤላ የአኙዋክ ዞን በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።

ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ ሆነው ይቆያሉ መባሉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!