Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በቱሪዝሙ ዘርፍ ለደረሰው ጉዳት መልሶ ማቋቋሚያ 13 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልገው ተለይቶ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በቱሪዝሙ ዘርፍ ለደረሰው ጉዳት መልሶ ማቋቋሚያ 13 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልገው ተለይቶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ባህል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የቱሪዝም አገልግሎቶች እና ምርቶች ልማት ባለሙያ ጥላሁን መዝገቡ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በክልሉ ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከ2011 ዓ.ም በፊት ከነበረው ጊዜ አንጻር ሲታይ በውስጣዊና ውጫዊ ተጽዕኖ ምክንያት ተዳክሟል፡፡

ለአብነትም ከ90 በመቶ በላይ ያህል ቱሪስቶች ከምዕራቡ ዓለም እንደሚመጡ ጠቁመው፥ ባለፉት ዓመታት ግን እንደ ክልልም ሆነ እንደሀገር በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ለጉብኝት አለመምጣታቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም ምርትና አገልግሎቶችን ለቱሪስቶች በመሸጥ መገኘት የነበረበት ገቢ ሳይገኝ ቀርቷል ነው ያሉት ባለሙያው፡፡

በነበረው ወቅታዊ ችግር ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ከ45 በላይ በቀጥታ ለዘርፉ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራትን፣  የቱሪዝም ምርትና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የተጎዱ የቱሪዝም አገልግሎቶችን ለማስጀመርም ከአማራ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማነቃቃት በቀጥታ ገንዘብ ተመድቦ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ÷ በክልሉ የሚገኙ 297 ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ ሁነቶች በልዩ ትኩረት እንዲከበሩ የክልሉ መንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጡንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ከ20 በላይ የሙያ ዘርፎችን ያካተተ የቱሪዝም አዋርድ በታህሳስ ወር እንደሚካሔድ ነው የጠቆሙት፡፡

በጥር ወር አጋማሽ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚመጡ የስነ ስዕል ባለሙያዎችን ያሳተፈ በዓባይ ወንዝ ላይ ያጠነጠነ ዐውደርዕይ በባሕር ዳር ከተማ ለማዘጋጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.