የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል 1 ሺህ 321 ሰዎች በሙስና ወንጀል ተከሰው ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

December 03, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሶስት ወራት ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ 1 ሺህ 321 ሰዎች ተከሰው ውሳኔ እንደተላለፈባቸው የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ አስታወቀ።

ውሳኔ የተሠጠባቸው ተከሳሾች ከአመት ከስድስት ወር እስከ 16 አመት የተፈረደባቸው ሲሆን፥ 230 ሺህ 554 ካሬ ሜትር መሬት ወደመሬት ባንክ ገቢ መደረጉንም ነው ያስታወቀው።

በተጨማሪም 70 ሚሊየን ብር፣ ሶስት መኪና እና ሶስት ዘመናዊ ቤቶች ለመንግስት ገቢ መደረጋቸውን የኦ ቢ ኤን ዘገባ ያመላክታል።

በአሁኑ ሰአት ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ 285 መዝገቦች በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጉዮ ዋሪዮ ከ289 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት፣ በተለያዩ ባንኮች የሚገኙ 67 ሚሊየን ብር እና ሠባት ቤቶች እግድ ተላልፎባቸው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው ካሉ አካላት መካከል የመንግሥት ባለስልጣናት፣ መሃንዲሶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ደላሎችና ባለሃብቶች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።