Fana: At a Speed of Life!

5ኛው ዙር በጎነት ለአብሮነት የበጎ ፍቃደኛ ወጣት ሰልጣኞች ምረቃ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ከባሕርዳር፣ ጅማ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን የሰላም መልዕክተኞች ዛሬ አስመርቋል፡፡

በሥነ ስርዓቱ ንግግር ያደረጉት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኝ በዩኒቨርሲቲው የቆዩ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ከ1 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ሰልጣኞች በ33 የሥልጠና ቀናት ውስጥ ሕብረተሰብን በበጎነት ማገልገልን እና ማሕበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሰላም መልዕክተኞቹ በሚሰማሩባቸው ክልሎች የሀገር በቀል ዕሴቶችን እንዲገበዩና ህብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንቱ እናንተ የዕለቱ ተመራቂዎች የዩኒቨርሲቲው አምባሳደር ናችሁ ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው÷ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በሰላም ዘርፍ የሚያደርጉት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

እንዲሁም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ‘በጎነት ለአብሮነት’ በሚል መሪ ሐሳብ በበጎነት ዙሪያ ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች ማስመረቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የሰላም ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር የሺ መብራት ”በጎነት በጊዜና በቦታ የማይወሰን ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናቸው ሲከታተሉ የነበሩ የብሔራዊ በጎፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት መርሐ ግብር ሰልጣኝ በጎፈቃደኞች መመረቃቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በፍቅረሚካኤል ዘየደ እና ወንድሙ አዱኛ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.