በወራቤ አንዲት እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆችን ተገላገሉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትናንትናው ዕለት በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንዲት እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆችን በሰላም ተገላግለዋል።
ወ/ሮ ነፊሳ ሸምሰዲን በስደት ከሚኖሩበት ሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ትውልድ ቀያቸው ሳንኩራ ወረዳ ዓለምገበያ ከተማ በጉዞ ላይ ሳሉ÷ በተሰማቸው ሕመም ምክንያት ወደ ወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያቀናሉ፡፡
በሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያዎች በተደረገላቸው ቀዶ ጥገናም÷ ሦስት ወንድና አንዲት ሴት ልጆችን በሰላም ተገላግለዋል፡፡
ወይዘሮ ነፊሳ ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ የወለዷቸው ሁለት ልጆች እንዳሏቸው አስታውሰው÷ በአሁኑ ሰዓት አራት ልጆችን በአንድ ጊዜ በመውለዳቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
የተወለዱት ሕጻናት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የሆስፒታሉ መረጃ አመላክቷል፡፡