Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ  መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ጊዜው አሁን ነው -ፕሮፌሰር ስቴፈን ዴርኮን

አዲስ አበባ፣ህዳር 25፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ጊዜው አሁን ነው ሲሉ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ስቴፈን ዴርኮን ተናገሩ፡፡

ፕሮፌሰሩ ከኮንቴክስት መፅሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ከሁለት ዓመታት የጦርነት ጊዜ ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ግጭት ለማቆም መስማማታቸውን አንስተዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው ይህ ስምምነት ሰላም ለማስፍን እና በጦርነቱ ከደረሰው የኢኮኖሚ ጉዳት ለማገገም  አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው÷ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሊደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ስቴፈን ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2018 ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማሳየቷን እና በዚህም የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል መሆኗን አብራርተዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ጦርነቱ ከመከሰቱ በፊት በቀጠናው በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ እንደነበረች ያነሱት ፕሮፌሰሩ÷ ከፈረንጆቹ  1998 እስከ 2020 የኢትዮጵያኢኮኖሚ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ በ 5 ነጥበ 4 በመቶ ብልጫ እንደነበረው አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁን ያለው የአይ ኤም ኤፍ የዕድገት ትንበያ እንደሚያመላክተው በጦርነቱ ምክንያት ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

በሀገሪቱ የደረሱ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ኪሳራዎችን ለመመለስ እና ኑሮን ለማረጋጋት የሰላም ግንባታ ጥረቶችን ማጠናከር እና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ድጋፎችን ማስቀጠል  አስፈላጊ መሆኑንም  አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትም ዓለም አቀፉ የገንዘብ  ተቋም  (አይ ኤም ኤፍ) ለኢትዮጵያ የብድር እፎይታን ሊሰጣት እደሚገባ እና የአፍሪካ ሀገራት የእድገት ዕድል ወደሆነው አጎዋ መመለስ እንዳለባት ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ባለ ሃባቶች ለኢኮኖሚ ማበረታቻ ድጋፍ በማድረግ መዋዕለ ንዋያቸውን  የሚያፈሱበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.