Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለ17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልክት አስተላልፈዋል፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

እንኳን ለ17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል (የኢትዮጵያዊነት ቀን) አደረሳችሁ።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል (የኢትዮጵያዊነት ቀን) ‹ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን› በሚል መሪ ቃል ይከበራል። ዘላቂ ሰላም የሚኖረን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጽናት ስንችል ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያለ ዘላቂ ሰላም፤ ዘላቂ ሰላምም ያለ ኅብረ ብሔራዊ አንደነት ሊሳካ አይችልም።

የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የኢትዮጵያዊነት በዓል ነው። ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦች የጋራና የአንድነት መገለጫ ነውና። ኢትዮጵያዊነት ማለት የብሔር ብሔረሰቦች ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ ቋንቋዎችና ጥበቦች በአንድነት የሚገለጡበት የጋራ ማንነት ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዓለም መድረክ አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ ከፈለግን ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበትን መንገድ መፍጠር አለብን። ጥያቄው እንዴት አድርገን ነው የምንፈጥረው የሚለው ነው።

ሁላችንም አሸናፊ መሆን የምንችለው ለሁላችን የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ስንችል ነው። ባለፉት ዘመናት አልተደረጉም የምንላቸውን ነገሮች ማድረግ የምንችለው ነገ በምንገነባት ኢትዮጵያ ነው። ባለፉት ዘመናት መደረግ አልነበረባቸውም የምንላቸውን እንከኖችም ማረም የምንችለው ነገ በምገነባት ኢትዮጵያ ነው። ለሁላችንም የምትሆነውን ኢትዮጵያ በትክክል መገንባት የምንችለው ሁላችንም ነገ ላይ ትኩረት ካደረግን ነው።

ይህችን ኢትዮጵያ የምንገነባው በሁለት የጥበብ መንገዶች ነው። የመጀመሪያው ከሁላችንም እንዲቀነስብን በመፍቀድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሁላችንም እንድናገኝ በማድረግ ነው። ለሌላው ወገናችን ህልውና፣ ሰላም፣ ክብር እና ፍትሕ ስንል የተወሰኑ ነገሮችን ከራሳችን ቀንሰን ለመሠዋት ፈቃደኞች መሆን አለብን። በጋራ መኖር የፈቃድ መሥዋዕትነትን ይፈልጋል። እንኳንስ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቀርቶ ባልና ሚስት እንኳን በጋራ ለመኖር ከፈለጉ ለትዳራቸው ሲሉ በጋራ የሚከፍሉት መሥዋዕትነት መኖር አለበት። ይህ መሥዋዕትነት ግን ሁላችን ለሁላችን የምንከፍለው መሆን አለበት።

በግዳጅ አንድን ነገር ማጣት ቅጣት ነው። ያለ ፈቃድ አንድን ነገር ማጣት ጭቆና ነው። ሰውን በግድ መንጠቅ ግፍና ጥቃት ነው። በፈቃድ የሚደረግ ማጣት ግን የጋራ ቤት ለመሥራት የሚከፈል ታሪካዊ ዋጋ ነው። ሌላው ወገናችን እንዲኖር፣ እንዲከብር፣ ሰላምና ፍትሕ እንዲያገኝ ስንል የምንከፍለው የፍቅር ዋጋ ነው። ይሄንን ዋጋ ለመክፈል ካልተዘጋጀን ከመተባበር ይልቅ መገፈታተር፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍ፤ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነት፤ ከመከባበር ይልቅ መሰባበር ዕጣ ፈንታችን ይሆናል። የምንናገረውን ነገር፤ የምንሠራውን ሥራ፣ የምናወጣውን ሕግ፣ የምንዘረጋውን አሠራር፤ የምናከብረውን በዓል፣ የምንሰጠውን ሹመት፣ የምናካፍለውን ሀብት፣ ለሌሎችም እንዲሆን አድርገን ስናከናውነው የምናጣው ነገር ይኖር ይሆናል። ይህ ግን አብሮ ለመኖር፤ አንድ ሀገር ለመገንባት፤ ለሁላችን የሚሆን ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተከፈለ ውድ ዋጋ ነው። ትውልድ ሁሉ ሲመካበትና ሲኮራበት የሚኖር ውድ ዋጋ ነው። በሌሎች መሥዋዕትነት ያልቆመ ማንም የለም።

ሁላችንም የመሥዋዕትነት ውጤቶች ነን። ለዚህ ነው እኛም ለሌሎች ስንል መሥዋዕትነት መክፈል ያለብን።

ለእኔ ብቻ ብለን በምንሠራው ነገር ለጊዜው ያሸነፍን፣ የበለጥንና ያተረፍን ሊያስመስለን ይችላል። ሌላውን አግልሎ እና ሁሉንም ጠቅልሎ ከአንድ ምእራፍ በላይ መጓዝ ግን አይቻልም። የሰው ልጅ በታሪኩ የኖረው ምድር ለእርሱ ብቻ እንድትመች እያደረገ ነው። ለእንስሳት፣ ለዕጽዋትና ለሌሎች አካላት ብዙ ትኩረት ሳይሰጥ ነው ዕድገቱን የቀጠለው።

በመጨረሻ ግን የተረዳው ነገር ቢኖር ብቻውን ሊኖር እንደማይችል ነው። ምድርን ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት፣ ለዕጽዋትና ለሌሎች ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ጭምር ምቹ እንድትሆን አድርጎ ካልተንከባከባት በቀር ሰው ብቻውን ደልቶት ምድር ላይ ሊኖር አይችልም። ሌላው ቀርቶ በዓይን የማይታዩ ፍጥረታት ጭምር ለሰው ልጅ ህልውና አስፈላጊ መሆናቸውንና ሰው ለእነርሱ ሲል ዋጋ መክፈል እንዳለበት ዘግይቶም ቢሆን ተረድቷል። የሰው ልጅ መድኃኒት እያጣላቸው የመጡ በሽታዎች የበዙት ሌሎችን አጥፍቶ ብቻውን ለመኖር ባደረገው የረዥም ጊዜ ትግል ምክንያት መሆኑን ከረፈደ ተረድቶታል።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣

በምንም መልኩ አንዳችን ያለ ሌላችን ልንኖር፣ ልናድግና ልናሸንፍ አንችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ሕዝቦች ሕዝቦቻችን ናቸው። ሁሉም ቋንቋዎች ቋንቋዎቻችን ናቸው። ሁሉም ባህሎች ባህሎቻችን ናቸው። ሁሉም በዓሎች በዓሎቻችን ናቸው። ሁሉም እምነቶች እምነቶቻችን ናቸው። ሁሉም ቅርሶች ቅርሶቻችን ናቸው። ሁሉም አካባቢዎች የሁላችን አካባቢዎች ናቸው። ሁሉም የተፈጥሮ ሀብቶች የሁላችንም ሀብቶች ናቸው። ለዚህም ነው በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የጸጥታ ኃይሎቻችን ደማቸውን የሚያፈስሱት፤ አጥንታቸውንም የሚከሰክሱት።

በተቃራኒውም እንዲሁ። የማንኛውም ብሔር መገፋት የኢትዮጵያ መገፋት ነው። የማንኛውም ወገን ቁስል የኢትዮጵያ ቁስል ነው። የማንኛውም ሕዝብ የትናንት ስብራት የኢትዮጵያ ስብራት ነው። የማንኛውም ሕዝብ መዋረድ የኢትዮጵያ መዋረድ ነው። የማንኛውም ሕዝብ መገደል፣ መፈናቀልና ሰላም ማጣት የኢትዮጵያ መገደል፣ መፈናቀልና ሰላም ማጣት ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ሰው ናት። እኛ ልጆቿ ደግሞ ልዩ ልዩ የሰውነት ክፍሎቿ ነን። ለአንዱ የሰውነት ክፍል የሚደረገው ነገር ሌላው የማይጎዳ መሆኑ መረጋገጥ ካልቻለ ጉዳቱ ዞሮ ይመጣል። አንዱን የሰውነት ክፍል አክብሮ ሌላውን አዋርዶ መሄድ አይቻልም። የአንዱ መታመም የሁሉም ሕመም ነው። አንዱ አካል ሲታመም ወደ ሕክምና የሚሄዱት ሁሉም አካላት ናቸው። እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችም እንደዚሁ ነን።

ዛሬ ከግላዊ ፍላጎታችን ላለፈ ለጋራ ፍላጎታችንና ለአንድነታችን እጅ የምንዘረጋበት ቀን ነው፤ ዛሬ በልዩነት ውስጥ ውበት ሳይሆን በልዩነት ውጥ ህይወት እንዳለ የምንመሰክርበት ዕለት ነው። ዛሬ ከማገር የተጣላ ጣሪያ መሆናችን ያከትማል። ዛሬ በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ የራሳችንን የማይተካ ቦታ እንይዛለን። ቤት በአገር ይመሰላል፡፡ ተነጣጥለን ከግብ እንደማንደርስ አውቀን በዕውቀት እና በፍላጎት ለጋራ ሕልውናችን በአንድነት እንቆማለን። አንዳችን ለአንዳችን መኖር የማናዳግም አማራጮች መሆናችንን ሳንዘነጋ እኩላችን ግርግዳ፣ እኩላችን ጣሪያ፣ እኩላችንም መዝጊያና መስኮት በመሆን አገራችንን ባማረ ሁኔታ እንገንባ።

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

የብርሃን እና የፍካት ጊዜያችን ደርሷል፤ በትዕግስትና ተስፋ ባለመቁረጥ የንጋት ደውላችንን እንደውል። ከግባችን ሳንደርስ መቆም ትልቅ ኪሳራ ያመጣልና ፍጥነታችንን ጨምረን መጓዛችንን እንቀጥል፡፡ ያላለቀ ጉዞ ከንቱ ድካም ነውና የድካማችንን ፍሬ የመብላት ጊዜው ሳይደርስ በፊት ጉልበታችን አይዛል።

የመንግስትነትና የታሪክ መሰረት የሌላቸው ሀገራት በአጭር ጊዜ ያማረ ሀገር እየገነቡ ባሉበት በዚህ ዘመን ላይ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ባለ ጠንካራ መሰረት ሀገር ይዘን የተጀመረውን መጨረስ ሊሳነን አይገባም፡፡ ሌሎች ሀገራት ዛሬ በሚያወጧቸው ሕጎች ሁሉን የሚያቅፍ ሥርዓት መገንባት ከቻሉ እኛ ከእነሱ በተሻለ በእሴት ጭምር የመገንባት ሀገራችንን ማጽናት እንችላለን። የባለ ጠንካራ መሰረት ህዝቦች መሆናችንን የመዘንጋት ጊዜያችን ያብቃ፤ ልዩነታችንን ለሚና ካዋልነው አንድነታችን በእሴታችን ላይ ባማረ መልኩ ይገነባል። አንድነት እና ልዩነት አይጣሉብን፤ ልዩነት ያልተደፈነ ቀዳዳችንን የምንደፍንበት የሥራ ስማችን ነው፤ አንድነት ደግሞ የእውቀት ጉዟችን ይሆናል። እናም በህብረት አንድ ላይ በመቆም ብቻ ሳይሆን በመደመር ኃይላችንን ከቁጥራችን እናብዛ።

ሁላችንም የምንጠቀምበትን ፍኖት ካልተለምን በአንድ ሀገር ውስጥ እየኖርን የብቻ ጥቅማችን ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ሁላችንም እኩል ካላሸነፍን፤ ማንም በዘላቂነት ሊያሸንፍ አይችልም። ሁላችንም ካልከበርን ማንም በዘላቂነት ሊከብር አይችልም። የምንሠራው እያንዳንዱ ሥራ ሌላውን የማይጎዳ፣ እንዲያውም ሌላውን ጭምር የሚጠቅም መሆኑን ርግጠኛ ካልሆን በስተቀር ልንሠራው አይገባም።

የምናስብበት መመዘኛ ሁለት መሆን እንደሚገባው ልብ እንበል። መላው ኢትዮጵያን አሸናፊ የማያደርግ ነገር ሁሉ ይዋል ይደር እንጂ ጉዳት ማስከተሉ እንደማይቀር እንወቅ። ከዚህ በተቃራኒ ተጉዘን ስኬታማ እንሆናለን በማለት የሚደረግ ሩጫ የሕልም ሩጫ ይሆናል። በግላችን ሮጠን ድህነትን ከመካፈል ውጭ የምናሳካው ብልጽግና አይኖርም።
በድጋሚ እንኳን ለኢትዮጵያውያን ቀን አደረሰን፤ መልካም የብሔር

ብሔረሰቦች በዓል!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሕዳር 29፣ 2015 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.