Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ያልተቋረጠ ውጤታማ ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሃመድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ ኢትዮጵያ አሸባሪውን የአልሸባብ ሃይል በመደምሰስ እና የሶማሊያን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በመደበኛ ስምሪት እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ሰራዊት በማሰማራት ከፍተኛ መስዋዕትነት ስትከፍል መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡
 
በዚህ መስዋዕትነት አንፃራዊ ሰላም ማግኘት በመቻሉ ፀረ አልሸባብ ትግሉ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
 
ኢትዮጵያ ከሌሎች አጋር ሀገራት ጋር በመሆን በሶማሊያ የምታደርገው ፀረ አልሸባብ ትግል ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም እና መረጋጋት ድርሻው የጎላ መሆኑን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ይህንን ትግል ውጤታማ ለማድረግ የሁለቱ ሀገራት በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።
 
ከመደበኛና ከሰላም አስከባሪ የሰራዊት ስምሪት በተጨማሪ የሶማሊያ መከላከያ ሃይልና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች አቅማቸውን ማሳደግ እና አስተማማኝ አቅም መፍጠር እንዲችሉ ለማድረግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እና አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
 
የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሃመድ ኑር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የሱማሊያ መንግስት እና ህዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ስታደርግ የቆየችው እና እያደረገች ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
 
በቀጣይም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ በማጠናከር ኢትዮጵያ የሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት አቅምን ለማጎልበት በስልጠና እና በአቅም ግንባታ ረገድ ተከታታይ ድጋፎችን እንድታደርግ ጠይቀዋል።
 
በሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሃመድ የተመራው የልዑካን ቡድን በቀጣይ ቀናት ከመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ጋር እንደሚወያይም የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.