Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ከፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታኅሳስ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ፓሲ ሂልማን ከተመራ የፊንላንድ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም በቀጣይ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ  መክረዋል፡፡

ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው÷ ኢትዮጵያና ፊንላንድ መልካም የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የፊንላንድ መንግስት በዓለም ባንክና በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል የሚያደርገውን የልማት ድጋፍ እንዲሁም በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመጠጥ ውሃና በሌሎች ዘርፎች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡

የፊንላንድ ባለሃብቶች በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሃይልና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ውጤታማ እንደሚሆኑ አመላክተዋል፡፡

የፊንላንድ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓሲ ሂልማን በበኩላቸው÷ ፊንላድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የሰብዓዊና የልማት ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

ግሎባል ጌት ዌይ በተሰኘው የአውሮፓ ህብረት የልማት ማዕቀፍ አማካኝነት ለታዳጊ ሀገራት በሚሰጠው የፋይናስ ድጋፍም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ የፊንላንድ ደርጅቶች እየተንቀሳቀሱ መሆኑንና በቀጣይም ሌሎች ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

ፊንላንድ ከአፍሪካ ሀገራት በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ እንደምትፈልግ መግለጻቸውንም  ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.