Fana: At a Speed of Life!

ለቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ልማት ፕሮጀክት የ10 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ፕሮጀክት ልማት የ10 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ፈቀደ።

የእንፋሎት ኃይል ልማት ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፉን ያገኘችው ባንኩ በዘላቂ የኃይል አቅርቦት አማራጮች ላይ ለሚሰሩ የአፍሪካ ሀገራት ይውል ዘንድ ከዓለም አቀፍ ግብረ-ሠናይ ተቋማት በድጋፍ የቀረበ ፈንድ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የገንዘብ ድጋፉን የአፍሪካ ልማት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ቡድን በጉዳዩ ላይ ከመከረ በኋላ ማፅደቁም ነው የተነገረው፡፡

በኢትዮጵያ የቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ፕሮጀክት ባንኩ በዘርፉ ድጋፍ ለማድረግ ያስቀመጠውን መሥፈርት አሟልቶ መገኘቱ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ እንዳስመረጠውም ነው የተገለጸው።

የቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ፕሮጀክት በፈረንጆች 2020 ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የ1 ነጥብ 55 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማግኘቱ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም 9 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ከእንፋሎት ኃይል አቅርቦት እና ሥጋት ቅነሳ አገልግሎት እንደተፈቀደለት ይታወሳል።

የእንፋሎት ኃይል አቅርቦት እና ሥጋት ቅነሳ አገልግሎት በምሥራቅ አፍሪካ በዘላቂ የኃይል አቅርቦት እና በእንፋሎት ኃይል ላይ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ሀገራት ድጋፍ በማበረታቻነት እንደሚያቀርብ ቲንክ ጂኦ ኢነርጂ ዘግቧል፡፡

የቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ በደቡብ ምሥራቅ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.