የሀገር ውስጥ ዜና

3ኛው የአፍሪካ ሴቶች የሰላምና ደኅንነት ፎረም መካሄድ ጀመረ

By Shambel Mihret

December 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሦስተኛው የአፍሪካ ሴቶች የሰላም እና ደኅንነት ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመክፈቻ መርሐ-ግብሩ ፕሬዚደንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በአፍሪካ በከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ እንዲሁም በሰላም ግንባታ ሂደት ተጽዕኖ ፈጣሪ ተግባራትን ያከናወኑ ሴቶች ተገኝተዋል።

ፎረሙ ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግን ያለመ ሲሆን÷ይሄንኑ ሚናቸውን እንዴት ማጠናከርና መደገፍ እንደሚገባ እንደሚዳስስም ነው የተነሳው።

እስከ ነገ በሚቆየው መርሐ-ግብር በሰላም ግንባታ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ እስትራቴጂዎችን መቅረጽ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙርያም ምክክር እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ በየሀገራቱ ያለውን ተሞክሮና ትስስር ማጠናከር ከመድረኩ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው ተብሏል።