Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት በጋዝ መሸጫ ዋጋ ጣሪያ ላይ መስማማት አልቻሉም

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኃይል አቅርቦት ላይ ሊወያይ በድጋሚ የተሰበሰበው የአውሮፓ ኅብረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አሁንም የጋዝ መሸጫ ዋጋ ጣሪያውን መቁረጥ አልቻለም ተባለ፡፡

ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ኅብረት የጋዝ አቅርቦት መሸጫ ዋጋውን በሜጋዋት ከ275 ዩሮ ወደ 220 ዩሮ በሰዓት ለመቀነስ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ ይህ ዋጋ አሁንም ከዓለም አቀፉ የመሸጫ ዋጋ የ35 ዩሮ ልዩነት አለው ነው የተባለው።

በአንጻሩ 12 የህብረቱ አባል ሀገራት በምክር ቤቱ የቀረበው ዋጋ እጅግ ውድ ስለሆነ ከ160 ዩሮ በታች በሆነ ዋጋ እንዲሸጥ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

መረጃውን ይፋ ያደረጉት የሃንጋሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ሺጃርቶ እንዳሉት ምንም እንኳን የኃይል ምክር ቤቱ ስብሰባ ዘለግ ያለ ክርክር ቢያስተናግድም በጉዳዩ ስምምነት ላይ ሳይደርስ ተበትኗል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ውይይቱን በሁለትዮሽ ደረጃ ለመቀጠል መታሰቡን ሺጃርቶ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

በጋዝ ዋጋ ላይ በ27ቱ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት የቀረበው የእርምጃ ሐሳብ አሁን ላይ ልዩነት ማስተናገዱንም ነው ያስታወቁት፡፡

እንደ ሀገራቱ ከሆነ የሚወሰደው እርምጃ አፈጻጸም የኃይል አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ይፈታል የሚል ሙሉ ዕምነት እንደሌላቸው አር ቲ ዘግቧል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የጋዝ አቅርቦት መሸጫ ዋጋ በሜጋዋት 292 ዶላር በሰዓት መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.