Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ስጋት የሆነውን ሙስና በዘላቂነት ለመከላከል ከዘመቻ ባለፈ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የደህንነት ስጋት እየሆነ የመጣውን ሙስና በዘላቂነት ለመከላከል፥ በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፀረ ሙስና ብሄራዊ ኮሚቴ አቋቁመው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይህ ብሄራዊ ኮሚቴ ወደ ስራ ገብቶ መውሰድ የጀመራቸውን እርምጃዎችንም አስታውቋል።

ክልሎችም መሰል ክልላዊ ኮሚቴ በማዋቀር እና አባላት በመሰየም በየራሳቸው ተንሰራፍቷል ያሉትን ሙስና ተከታትለው ለመግታት፤ ሙሰኞችንም ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሰሩ እየገለፁ ይገኛሉ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ አቶ ፍሬው ካሳዬ፥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሙስና በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ከመንሰራፋቱ ባለፈ የደህንነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡

በተለይም በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚታየው ሙስና ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ያነሱት መምህሩ፥ በእነዚህ ተቋማት ላይ አገልግሎትን በገንዘብ መግዛት የተለመደ መሆኑን ነው የሚያነሱት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ መምህሩ ዶክተር ኮማንደር ደመላሽ በበኩላቸው፥ ሙስና ከሽብር ድርጊት ባልተናነሰ ሁኔታ ሀገርን የማጥፋት አቅም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው ሙስና ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ በላይ በመዋቅር ትስስር እና በህገ ወጥ ሰንሰለት የሚፈጸመ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል ነው የሚሉት፡፡

ሙሰኛ ባለስልጣናት ግጭት ወደ መጥመቅ እንዳይሸጋገሩ ስለ መስራት

ሙስና በሀገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል መንግስት የጀመረው እርምጃ የሚደነቅ ነው የሚሉት ምሁራኑ፥ ይሁን እንጂ በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና ግለሰቦች ዘመቻውን እንዳያደናቅፉ በጥንቃቄ መመራት አለበት ባይ ናቸው።

ለአብነትም በትላልቅ የሙስና ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ እና እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የገመቱ ባለስልጣናት አይነኬ የሆኑ ሃሳቦችን በማንሳት ግጭት ለመጥመቅ እና ሀገርን ለማተራመስ ሊሰሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ይህን ችግር ለማስወገደም በሙስና የሚጠረጠሩ ዜጎች ላይ አስፈላጊውን ማስረጃ በፍጥነት በማሰባሰብ ተገቢውን እርምጃ በጊዜ መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ሙስናን በዘላቂነት ለማስወገድም ለሙስና የሚመቹ መዋቅሮችን፣ መመሪያዎችን እና ደንቦችን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፥ ከሁሉም በላይ ግን የመንግስት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሀዋሳው የብልፅግና አስቸኳይ ጉባኤና አቅጣጫዎቹ

መሪው ፓርቲ ብልጽግና በሀዋሳ ከተማ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋውን ሙስና ለመታገል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

ፓርቲው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሃላፊነት በመዘንጋት ዜጎችን ለአላስፈላጊ እንግልት እና ወጪ የሚዳርጉ ሙሰኛ የስራ ሃላፊዎችን ያለ ምህረት እርምጃ እንደሚወሰደ ነው የገለጸው፡፡

ለአብነትም ሰሞኑን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር፣ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን ማንሳት ይቻላል፡፡

ምሁራኑ፥ የመንግስት አገልግሎትን ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ማህበረሰቡን ለከፍተኛ ምሬት ዳርገዋል እንዲሁም የመንግስትን ንብረት መዝብረዋል በተባሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለሕግ መቅረብ መጀመራቸው የሚበረታታ ተግባር ነው ይላሉ፡፡

ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት ችግሩን ከመረዳት ባለፈ ለተግባራዊነቱ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆኑ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም መንግስት በራሱ መዋቅር እና ስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችን ጨምሮ ሁሉንም በወንጀሉ የሚጠረጠሩ ሙሰኞችን ተጠያቂ ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይሁን እንጂ ጅምር እንቅስቃሰሴውን ተከትሎ በከባድ ሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ባለስልጣናት ያላቸውን መዋቅር እና ስልጣን እንዲሁም ገንዘብ ተጠቅመው መረጃ እንዳያሸሹ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት ምሁራኑ፡፡

መንግስት ሙስናን ለመከላከል ያቋቋም ኮሚቴ ስኬታማ እና ተዓማኒ እንዲሆን ገለልተኛ የሆኑ አካላትን ማሳተፍ እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

የተጀመረው የሙስና ትግል ማህበረሰበ መር መሆን አለበት የሚሉት ምሁራኑ፥ ዜጎች ለሚያገኙት አገልግሎት ገንዘብ አለመስጠት እና ሙስና የሚጠይቅ ሲያጋጥም ለሚመለከተው አካል መጠቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.