Fana: At a Speed of Life!

በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች ለ6 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰብዓዊ ድጋፍ በሶስቱም ክልሎች 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን የሚኒስትሮች ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ኮሚቴው ዛሬ ባደረገው ስብሰባ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን የገመገመ ሲሆን÷ በሰብዓዊ ድጋፍ በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በሶስት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ እንደሆነ የገለጹት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም÷ በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ መሰረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የህዝብ ተቋማትን የማስጀመር ስራዎች ተጠናክረው እየተሰሩ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በመሰረታዊ አገልግሎቶችም ስልክ፣ ኤሌክትሪክ፣ ባንክ እና የአየር ትራንስፖርት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት በበኩሉ÷ በ57 ከተሞች/ዞኖችና/ወረዳዎች አገልግሎት ለማስጀመር ታቅዶ እስካሁን 41 የሚሆኑ ከተሞች/ዞኖችና/ወረዳዎች ላይ አገልግሎት ማስጀመሩን ገልጿል።
እስካሁን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል በጦርነቱ ከወደመው የኤሌትሪክ መስመር 85 በመቶ ያህሉን ጥገና አድርጓ ተብሏል፡፡

ኢትዮ ቴሌም በትግራይ ክልል 65 የቴሌኮም ስቴሽኖችን ማስጀመሩ እና 1 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር የኦፕቲካል መስመር ጥገና ለማድረግ ታቅዶ 825 ኪሎ ሜትር የሚሆነው እስከተያዘው ሳምንት ድረስ መጠገኑ ተመላክቷል፡፡

የመድሃኒት እና የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራ÷ ወደ ሽረ፣ አላማጣና መቀሌ በመኪና እና አየር ትራንስፖርት የጤና ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የተቋረጡ ትምህርቶችን መልሶ በማስጀመር በኩልም በአማራና አፋር ክልል 28 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እና 687 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መልሶ ማስጀመር መቻሉ ተገልጿል፡፡

አክሱምና ራያ ዩኒቨርሲቲዎችን ትምህርት ለማስጀመር ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉንና በቀጣይ የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት መደረጉም ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም የፈረሱ ሁሉንም ድልድዮች መልሶ በመጠገን ሁሉም መንገዶች አሁን አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የተቋረጡ በረራዎችን መልሶ ለማስጀመር ሙሉ ዝግጅቴን አጠናቅቄአለሁ ብሏል፡፡

ሰራተኞችን ወደስራ መመለስ የነዳጅ እጥረት ተጨማሪ በጀት ማፈላለግ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው እንደሚገባ የቴክኒክ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

በቀጣይም አሁን በስራ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በአጭር ጊዜ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ ተገልጿል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.