Fana: At a Speed of Life!

እስካሁን በአማራ እና አፋር ክልሎች 209 ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ አልተመለሱም

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭቱ ምክንያት በደረሰባቸው ውድመትና ከፊል ጉዳት እስካሁን በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚገኙ 209 የትምህርት ተቋማት ወደ አገልግሎት አለመመለሳቸውን የየክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች አስታወቁ፡፡

በክልሎቹ ከሦስተኛው ዙር ግጭት በፊት በ4 ሺህ 365 የትምህርት ተቋማት ላይ በተፈጸመ ውድመትና ከፊል ጉዳት በጊዜው በነበረ የገበያ ሁኔታ 8 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ኪሳራ መድረሱ ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወንድወሰን አቢ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ከሦስተኛው ግጭት በፊት በ1 ሺህ 151 የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ በ2 ሺህ 935 ደግሞ በከፊል በደረሰው ጉዳት ከ6 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ኪሳራ ደርሷል፡፡

10 የትምህርት ተቋማት ግንባታቸው ተጠናቆ ሥራ መጀመራቸውን እና 78 ደግሞ ግንባታቸው ሊጀመር በሂደት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

እስካሁን 159 ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ አለመመለሳቸውን እና በቀሪዎቹ ደግሞ ከሞላ ጎደል መጀመሩን ጠቁመው÷ አሁን የተሰጠው መፍትሔ ከደረሰው ጉዳት አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ለማቅረብ ታስቦ÷ እስካሁን የምገባ አገልግሎቱ የተጀመረው ለ160 ሺህ 543 ተማሪዎች ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ይህም የትምህርት ማቋረጥን ለመቀነስና ጥራትን ለማሳደግ ለሚከናወነው ሥራ ክፍተት እንደሚፈጥር አመላክተዋል፡፡

የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አሕመድ ያዬ በበኩላቸው፥ በክልሉ 96 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ 183 ደግሞ በከፊል መጎዳታቸውን እና ጉዳቱ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሆኑን ነው የገለጹት።

እስካሁን 229 ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መጀመራቸውን እና 50ዎቹ ወደ ሥራ አለመመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ለትምህርት ተቋማቱ፣ ለመምህራንና ለተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ትምህርት መጀመሩን፤ በዓለም የምግብ ፕሮግራምና በተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት በኩል ለተማሪዎች ምግብ እየቀረበ መሆኑን አክለዋል፡፡

የወደሙ የትምህርት ተቋማት እስከሚገነቡ ለጊዜው ድንኳን በመጣል ትምህርቱ መጀመሩንና ከፊል ጉዳት የደረሰባቸው ተጠግነው መደበኛው መማር ማስተማሩ መቀጠሉን አረጋግጠዋል፡፡

ባለፈው ሐምሌ ወር የነበረው ግጭት የጉዳት መጠን የጥናት ውጤት ይፋ ሲደረግ ጉዳቱ እንደሚጨምር ጠቁመው አጋር አካላት፣ የተራድዖ ድርጅቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ የሥራ ኃላፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞች እና ጥራት መሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ ወጋሶ እንደገለጹት÷ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት እስከ ሦስት ዓመታት ትምህርት በተቋረጠባቸው የአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች ልዩ የትምህርት ፕሮግራም ተዘጋጅቷል፡፡

ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮ የባለሙያዎች ቡድን ወደ አካባቢዎቹ እንደሚያቀና እና ቡድኑ በሚያካሂደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት የትምህርት ዘርፍ ምላሽ ይተገበራል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር በተያዘው ዓመት 200 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን፤ የ50 ትምህርት ቤቶች ዲዛይን መጠናቀቁን እና የአምስት ትምህርት ቤቶች ግንባታ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን አረጋግጠዋል፡፡

ከትምህርት ቁሳቁስ ጋር በተያያዘም 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው የትምህርት ቁሳቁስ አሰራጭተናል፤ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግም በሂደት ላይ ነን ብለዋል አቶ ዮሐንስ፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.