የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ የአፍሪካ ሰብዓዊ ኤጀንሲን ለማቋቋም ስላለው ጥረት መከሩ

By Alemayehu Geremew

December 15, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ የአፍሪካ ሰብዓዊ ኤጀንሲን ለማቋቋም ስላለው ጥረት ለአፍሪካ ኅብረት እና ለተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዳይሬክተር ጋር መክረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ÷ በአፍሪካ የሥነ-ሕዝብ ዕድገት ፣ እንዲሁም በትምህርትና በጤናው ዘርፍ አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ከኮሚሽኑ ዳይሬክተር ማቤንጌ ንጎም ጋር መምከራቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በውይይታቸው የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በተለይ ለልጆገረዶች ለማቅረብ በሚገጥሙ ተግዳሮቶች ላይም እንደመከሩ ከፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በአሜሪካ የሚኘው ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ያቋቋመው የ”ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” መሥራቾች ከሆኑት አንዱንና የድርጅቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍሥሃ እሸቱ በጽኅፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ድርጅቱ በኢኮኖሚ ልኅቀት ለማምጣት፣ ረሃብን ለመዋጋት ብሎም የገበሬውን የአኗኗር ሥርዓት ለመለወጥ በግብርና፣ በኢ- ኮሜርስና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ድርጅቱ ‘ኑ አብረን እንሥራ’ የሚል አክሲዮን እንደሚያንቀሳቅስም በመረጃው ተመልክቷል፡፡

ፕሬዝደንት ሣኅለወርቅ ዘውዴም ድርጅቱ እየሠራ ስላለው ሥራ አመስግነው ጥረታቸውን እንደሚደግፉ በመግለጽ አበረታተዋቸዋል።