የሀገር ውስጥ ዜና

የባህልና ቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን ስምምነት ተፈረመ

By Meseret Awoke

December 15, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ እና የአማራ ብሔራዊ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ጣሂር መሃመድ ተፈራርመውታል፡፡

ዶ/ር በለጠ ሞላ ፥ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የሆነውን እምቅ ሃብት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን ገበያውን በማሳደግ ለሀገራችን ሊያበረክት የሚገባውን ኢኮኖሚ እንዲያበረክት ተቀናጅቶ መስራቱ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ክልል በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል ያሉት ሚኒስትሩ ፥ ቱሪዝሙን በማሳደግ በቀጣይ የሚመጣውን ውጤት እያየን ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚ እንድታገኝ የሚያስችል አቅም እንዲፈጠር በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በበኩላቸው ፥ የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገራችን ኢኮኖሚ የሚጠበቀውን ያላበረከተው መሰራት ያለበት ስራ ባለመሰራቱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የዲጂታል ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የባህልና ቱሪዝም የመዳረሻ ስፍራዎችን የማስተዋወቅና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር መሰራት እንዳለበት መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የቱሪዝሙን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ቴክኖሎጂ መር አገልግሎት በማበልፀግ የተገልጋይን እርካታ፣ የዘርፉን እሴት ሰንሰለትና የአገልግሎት ጥራት ለማዘመን የስምምነት ፊርማው በቀጣይ ከሌሎች ክልሎች ጋር እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡