የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ማንም አዝማች ማንም ዘማች የለም – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ማንም አዝማች ማንም ዘማች የለም፣ ሁሉም ዘማች፤ ሁሉም በሃላፊነት የሚንቀሳቀስበት ወቅት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋመው ንዑስ ኮሚቴ እስካሁን ድረስ ባከናወናቸው ስራዎች ላይ ዝርዝር የአፈጻጸም ሁኔታ ግምገማዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዝርዝር የአፈጻጸም ግምገማው ላይ በመመስረት ለወደፊቱ ምን መደረግ እንዳለበትም አቅጣዎች መቀመጣቸውንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከገባ 19 ቀናት የተቆጠሩና 25 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥ ሁለቱ ከበሽታው ማገገማቸውንና እስካሁን ምንም የሞት አደጋ አለማጋጠሙን አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
ነገር ግን ከወረርሽኙ ባህሪ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምንመለከተው እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ ሁኔታ አኳያ በኢትዮጵያም ቢሆን የበለጠው አደጋና የበለጠው ችግር እንዳይመጣ መዘጋጀትና መረባረብ የሚጠይቅበት ሁኔታ ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት።
በተለይ ደግሞ ቀደም ባሉት ቀናት በአብዛኛው በቫይረሱ የተያዙት በአዲስ አበባ አካባቢ የነበሩ ሲሆን፥ አሁን ግን ወደ ክልሎችም ተስፋፍቶ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መታየት መጀመራቸው ወረርሽኙ ወደ ውስብስብ ችግርና ጉዳት እንዳይደርስ ህዝባችንና መንግስታችን ሁሉም ተቀናጅተው ርብርባቸውን ማጠናከርና መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በእንደዚህ አይነት ወቅት አዝማችና ዘማች የለም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሁሉም ዘማች እና በሃላፊነት መንቀሳቀስ የሚገባበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።
አያይዘውም መንግስት የአለም አቀፍ ተሞክሮን እና የህክምና ስርዓቱን በመከተል ከወረርሽኙ ባህሪ አኳያ በጤና ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ምን ምን ጥንቃቄዎች መደረግና መሰራት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ልዩ ልዩ አቅሞችን ተጠቅሞ ለማሳየት እንደሞከረ አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ በዚህ ደረጃ የሚያደርገውን ጥሪ እየተከተለ ምላሽ ለመስጠት እያደረገ ያለው መነሳሳት የሚያበረታታ ቢሆንም ፥ ከችግሩ አሳሳቢነት እና ውስብስብነት የተነሳ በቂ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል አይደለምም ብለዋል።
የበለጠ መዘጋጀትና ይህንን አደጋ ሊመክት የሚችል ታሪካዊ ወቅት ላይ መኖር ይገባናል፤ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሳምንታት የጤና ባለሙያዎቻችን ባልተመቸ ሁኔታ ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ስለሆነ ይህ ድርጊታቸው በእጅጉ የሚያኮራና የሚያበረታታ ነው ሲሉም አመላክተዋል።
በተመሣሣይ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የወጣቶች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተነሳሽነትና ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴን አቶ ደመቀ አድንቀዋል።
መንግስት የመሪነት ሚናውን የበለጠ በክልልና በፌደራል ደረጃ በማሳለጥ ሚናውን መጫወት ይገባዋልም ብለዋል።
ከዚያም ባለፈ ህብረተሰቡም በልዩ ልዩ መስክ የሚሰጡ ትምህርቶችን በአግባቡ ቆጥሮ በመውሰድ፣ ከግለሰብ ከራስ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ድረስ አገርንና ትውልድን ዜጋን የመታደግ ሉዓላዊነትን የማስከበር ጉዳይ ስለሆነ ይህንን ጥብቅ የሃላፊነት ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት።
በዚህ ግምገማ በመጪው ቀናት ምን ላይ አተኩረን ማስተካከልና ማረም ብሎም የመከላከል አቅማችንን ማጎልበት እንችላለን የሚለውን በዝርዝር ለማየት መሞከሩን አስታውቀዋል።
በዚህም አንደኛውና አሁን ጎላ ብሎ እንደ ክፍተት የሚታየው በፌደራል መንግስትና በክልሎች መካከል የሚወሰኑ ወረርሽኙን የመከላክል ስራዎች የተናበቡና የተመጋጋቡ ስላልሆኑ፥ በፌደራል እና በክልል ያሉ የመንግስት አካላት በዚህ ደረጃ ግንኙነታቸውን ማጠናከርና ወጥና ተመጋጋቢ የሆነ ስርዓት መዘርጋት አለባቸው ነው ያሉት።
ለዚህም ሲባል የክልልና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች ተከታታይ የሆኑ ግንኘኙነቶችን እያደረጉ ከዳር እስከ ዳር ሀገርን የመታደግ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በ2ኛ ደረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 87 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች የሚያደርገውን በረራ ማቆሙን በማንሳት እና በረራ ካልተቋረጠባቸው ሀገራት ወደ ሀገራቸው የሚመጡትን በመቀበልና ለለይቶ ማቆያነት ወደ ተመደቡ ሆቴሎች የመውሰዱን ስራ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከሀብት ማሰባሰብ ጋር በተያያዘ በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስና ወደፊት ለመራመድ የሚያስችለው አቅም እንዲኖረው ማድረግ እና በህብረተሰቡ ዙሪያ ለመረዳዳትና ለመደጋገፍ ያለውን ፍላጎት በተቀናጀና ወጥ በሆነ ስርዓት መምራት ስለሚያስፈልግ የገቢ ማሰባሰብና የምግብ ክምችት ስርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።
ለዚህም እስካሁን ድረስ ህብረተሰቡ በውጪም ሆነ በሀገር ቤት ለገቢ ማሰባሰብ ስራ የሰጠው ትኩረትና ያለውን እያካፈለ ይህንን ጊዜ ለመሻገር ያለው ቁርጠኝነት የሚያኮራና የሚያበረታታ በመሆኑ የሀብት አሰባሰብ ስርዓታችን በጥንቃቄና በሃላፊነት ለቁርጥ ቀን እና ለባሰ ቀን ለማዋል የሚያስችለን አቅም መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ አጭር ጊዜም የተሰባሰበው ሀብት የሚያሳየው እንደሀገር ብዙ ሀብት መፍጠር እንደምንችል በማሳየቱ ስርዓቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ብዙ ድሃ ወገኖቻችን የእለት ማደሪያና ውሎ መግቢያ የሌላቸውን የሚታደግ ስራ ለመስራት የመጠባበቂያ ክምችት አቅምን ለመገንባት የሚያስችል ስራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዓለም ያለው አስከፊ እና አስፈሪ ሁኔታ በርቀት የምናየው ሳይሆን በደጃችን ደርሷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሳንደናገጥ ከራሳችን ጀምሮ ቤተሰብንና ህብረተሰብን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በገበያ ስፍራዎች፣ በሀይማኖት ተቋማት እና በመሳሰሉት ስፍራዎች እርቀትን በመጠበቅና የአለም የጤና ድርጅት ቆጥሮ ያስቀመጣቸውን መመሪያዎች በመከተል ተግባራዊ እንዲደረግ አሳስበዋል።