Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የመስተንግዶ ሰራተኞች ከሀገር ባህል የወጣ አለባበስ እንዲለብሱ በሚያስገድዱ ሆቴሎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመስተንግዶ ስነ-ምግባር እና ከሀገር ባህል የወጣ አለባበስ ሰራተኞቻቸው እንዲለብሱ በሚያደርጉና በሚያስገድዱ ሆቴሎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በመዲናዋ በሚገኙ ባለ ኮከብ ሆቴሎችና ሌሎች የዘርፉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአስተናጋጅነት ለእንግዶች አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች አለባበስ የመስተንግዶ አገልግሎት አሠጣጥ ሥራ ስነ-ምግባርን ያከበረ አይደለም፡፡

በእነዚህ ተቋማት ከኢትዮጵያ ባህልና ዕሴት የወጣ እንዲሁም የመስተንግዶ አገልግሎት ዘርፍን ደረጃን ያልጠበቀ አለባበስ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ፈቃድ ሲያወጡ የቱሪዝም የስነ ምግባር ኮድ የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ያስገድዳል ያሉት ሃላፊዋ፥ በዚህም የሀገሪቱን ባህል፣ ወግ እና እምነት መጠበቅ የመጀመሪያው ሃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መሰል ድርጊቶች የሚስተዋሉት በብዛት ማታ ላይ መሆኑን ጠቁመው፥ ተቋማቱ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለሆቴል ባለ ንብረቶች ንግድ ዘርፍ ማህበር የማሳሰቢያ ደብዳቤ መላኩን ነው የገለጹት፡፡

ስለሆነም ከመስተንግዶ ስነ-ምግባር እና ከሀገር ባህል የወጣ አለባበስ ሰራተኞቻቸው እንዲለብሱ በሚያደርጉና በሚያስገድዱ ባለ ኮከብ ሆቴሎች፣ ባለኮከብ ሬስቶራንቶች፣ ተመራጭ ፣ ከፍተኛ፣ እነስተኛ ደረጃ የሚገኙ ሆቴሎች ፣ ሬስቶራንቶች ፣ ባሮች ፣ ካፌዎች እና ፔኒሲዮኖች ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የወጣውን መስተንግዶ ስነ ምግባር ኮዱ ተፈጻሚ እንዲያደርጉም በቢሮው መዋቅር እስከ ወረዳ ድረስ የቁጥጥር እና ክትትል ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከከተማው ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ጋር በተለይም ማታ ላይ አስተናጋጆች ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠ አለባበስ እንዲለብሱ የሚያደርጉ ተቋማትን በመለየት እርምጃ እንደሚወሰድ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.