Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በ1 ሺህ 300 ወረዳዎች የምክክር ተሳታፊዎች ልየታ ሊያካሂድ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ1 ሺህ 300 ወረዳዎች የምክክር ተሳታፊዎች ልየታና ምዝገባ በቅርቡ እንደሚጀምር የኮሚሽኑ አመራሮች ገለጹ።
 
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ኂሩት ገብረሥላሴና ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው÷ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት ስለምክክር ሂደቱ፣ ስለተሳታፊዎች ልየታ የሃሳብ ግብዓት የመሰብሰብ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
 
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ኂሩት እንዳሉት÷ ኮሚሽኑ አካታችና አሳታፊ ምክክር የማካሄድ ኃላፊነት ስላለበት በየክልሎቹና በከተማ አስተዳደሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ግብዓት የመሰብሰብ ስራ በመጠናቀቅ ላይ ነው።
 
በዚህም ከፊል አዲስ አበባና ከፊል ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ባለድርሻ አካላትን አወያይቶ ግብዓት የመሰብሰብ ስራዎች እንደቀሩ ጠቁመው÷ እነዚህም በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቁ አስረድተዋል።
 
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ያላት ሀገር እንደመሆኗ ሁሉም ማህበረሰብ በተወካዮቹ በኩል እንደሚሳተፍም ነው የተናገሩት።
 
የባለድርሻ አካላትን አስተያየት በመሰብሰብና መተማመን ላይ በመድረስ ምክክር ከተካሄደ ቅቡልነት እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
 
የኮሚሽኑ አመራሮች አክለውም÷ ሙሉውን የኢትዮጵያ ህዝብ በምክክሩ ለማሳተፍ ስለሚያስቸግር ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተወከሉባቸው ተሳታፊዎች መረጣ ይካሄዳልም ነው ያሉት።
 
የተሳታፊዎች ውክልና እንደየ ክልሎቹና ማህበረሰቡ ሁኔታ ዝርዝር መስፈርት እንዳለውና ሁሉም ማህበረሰብ እንዲወከል የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
ምክክሩ በሁሉም ወረዳዎች ስለሚደረግ በልየታው ውስጥ ምንም ዓይነት ችኮላ ሳይኖር በጥንቃቄ ሁሉም ማህበረሰብ እንዲወከል ይደረጋል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.