የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የጤና በረከቶች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የበሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እና ጤናማ ህይወት ለመምራት ከሚያስችሉ ቀላል መንገዶች አንዱ ነው፡፡
መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደ ደም ግፊት ፣ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ)፣ የስኳር ህመም፣ ድብርት፣ ጭንቀት፣ የተለያዩ አይነት የካንሰር በሽታንእና ሌሎች በርካታ የጤና ችግሮችን እና ስጋቶችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡
በተጨማሪም በእነዚህ እና ሌሎች ከባድ እና ስር የሰደዱ በሽታዎች የመሞት እድልን እንዲቀንስ እንደሚያደርግ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ኦክስጅንን እና አልሚ ምግቦችን ወደ ጡንቻ እንዲደርስ ስለሚረዳ የልብና የደም ዝውውር ሥርዓት እንዲሻሻል ያደርጋል፡፡
የልብን እና የሳምባን ጤንነት በማሻሻል የዕለት ተዕለት ስራዎችን ለመከዎን የበለጠ ጉልበትም ይፈጥራል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ከሚገኙ የጤና በረከቶች ውስጥ
የማስታወስ ችሎታችን መጨመር እና የአንጎል ስራን ለማሻሻል፤
ከበርካታ ከባድ በሽታዎች ራስን ለመከላከል፤
ክብደትን በመቀነስና በመቆጣጠር ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎች ለመቆጣጠር፤
የእንቅልፍ እጦትን ለመከላከል፤
በጭንቀት እና ድብርት የመጠቃት እድልን ለመቀነስ፤
የመገጣጠሚያ አካባቢ ህመምን ለመከላከል፤
የጡንቻ ጥንካሬን በመሳደግ ሚዛንን ለመጠበቅ፤
የአካል ብቃት ጥንካሬን ለመጨመር ይረዳል።
ምንም እንኳን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በርካታ የጤና በረከቶች ቢኖሩትም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ባለሙያ አማክረው ቢሆን ይመረጣል፡፡
በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አልያም ከ4 ሺህ እርምጃ ያላነሰ የእግር ጉዞ በማድረግ ጤናን መጠበቅ እንደሚቻል የሜዲካል ዌብ መረጃ ያመላክታል።