የሀገር ውስጥ ዜና

የኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ የህብረት ስራ ማህበራት ቀንን እያከበረ ነው

By Amele Demsew

December 16, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ የህብረት ስራ ማህበራት ቀንን እያከበረ ነው፡፡

ባንኩ “ኅብረት ስራ ማህበራት ለተሻለ ዓለም ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ነው ቀኑን እያከበረ የሚገኘው።

በመርሐ ግብሩ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኃላፊ መሰረት አሰፋ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት ደሪቤ አስፋው፣ ጀማሪ የህብረት ስራ ማኅበራት፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ደርቤ አስፋው÷ ለአርሶ አደሩ ባንኩ ከሚሠጠው የብድር አገልግሎት ጎን ለጎን አንድ በመቶ ዓመታዊ ትርፉን ለስልጠና የሚያውል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባንኩ ለአርሶ አደሮች ልዩ የቁጠባ ሒሣብ በማዘጋጀት ሚሊየኖችን ተጠቃሚ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ ለሦስት ዓመታት ያህል የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀንን ሲያከብር መቆየቱን ጠቁመው÷ የዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜው ነው ብለዋል፡፡

በባዕሉ ባለፈው ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የህብረት ስራ ማህበራት ሽልማትና እውቅና መሰጠቱም ተገልጿል፡፡

በቤተልሄም መኳንንት