አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፎችን የማድረግ እቅድ አላት – ፖሊቲኮ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፎችን ለዩክሬን የማድረግ እቅድ እንዳላት ፖሊቲኮ አስነበበ።
ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ስድስት ሰዎች ዋቢ ያደረገው የፖሊቲኮ ዘገባ እንደሚያስረዳው ዋሺንግተን የዩክሬንን ወታደራዊ አቅም የሚያጠናክሩ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፎችን የማድረግ እቅድ አላት።
የዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ ሃላፊዎች ሩሲያ በክረምቱ ወቅት ለከባድ ጥቃት ተዘጋጅታለች ማለታቸውን ተከትሎ ዋሺንግተን ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ አቅዳለችም ነው ያለው ዘገባው።
ወታደራዊ ድጋፉ ፓትሪዮት ከተሰኘው ዘመናዊ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ በተጨማሪ የሚደረግ ሲሆን፥ ዘመናዊ የጦር ተሽከርካሪዎችንም ያካተተ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም መሬት ለመሬት ተተኳሽ ቦምቦች እና እስከ 150 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች፣ የአጭርና መካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችና “ስማርት ቦምቦችን” በድጋፉ ለማካተት የቀረበውን ሃሳብ የባይደን አስተዳደር እያጤነው መሆኑንም ነው ዘገባው ያመላከተው።
ይህ ድጋፍ ሩሲያ ከከባዱ ክረምት በፊት የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ ትጀምራለች በሚል ከዩክሬናውያን ባለስልጣናት ዘንድ የቀረበውን የስጋት ሃሳብ መነሻ ያደረገ ስለመሆኑም ነው የተገለጸው።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የተባለው ድጋፍ ዩክሬን ምድር የሚገባ ከሆነ የሩሲያ ኢላማ ይሆናል ብለዋል።
ሩሲያ ቀደም ብላ አሜሪካ ዘመናዊ ፀረ ሚሳኤል ለዩክሬን ካቀረበች አፀፋዊ ምላሽ እወስዳለሁ ስትል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ከድጋፉ ባለፈም አሜሪካ በጀርመን በሚገኘው የጦር ሰፈሯ ለዩክሬን ጦር ተጨማሪ ስልጠናዎችን እሰጣለሁ ማለቷን አር ቲ ፖሊቲኮን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሐሙስ እለት የፔንታገን ፕሬስ ሴክሬታሪ ብርጋዴር ጄኔራል ፓትሪክ ራይደር በጀርመን በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ለዩክሬን ጦር የስልጠና መርሐ ግብር በስፋት እንደሚጀመር ተናግረዋል።
አሜሪካ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ 3 ሺህ 100 የዩክሬን ወታደሮችን ማሰልጠኗ የሚታወስ ሲሆን፥ በአዲሱ እቅድ መሰረትም በየወሩ የሚሰለጥኑ ወታደሮች ቁጥር ወደ 500 ከፍ እንደሚል ገልጸዋል።