Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 23ኛው በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም መካሄድ ጀመረ።
ጉባኤው “ጠንካራ አጋርነት ለመልሶ መቋቋም፣ መልሶ ግንባታና ለሁለንተናዊ ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ነው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው።
ጉባኤውን ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በሚያከናውኗቸው ተግባራት የክልሉን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ክልሉ በወረራና ጦርነት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ችግሩን ለማስወገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛና ድጋፍ ቀላል እንዳልነበር ነው ያስታወሱት።
በቀጣይም የክልሉ መንግስት በሚያካሂዳቸው የልማትና የእድገት ጉዞዎች ዩኒቨርሲቲዎች በእውቀትና ክህሎት ላቅ ያለ ሚናን እንዲጫወቱ ጠይቀዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ይዟቸው የተነሳ አላማዎች እንዲሳኩና ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ልዩ ልዩ የለውጥ ተግባራት ተቋማቸው ከፍተኛ ሚናን ሲጫወት እንደቆየ ጠቁመው፥ ወደፊትም ይህንኑ የትብብር ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት፥ ፎረሙ በክልሉ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ነበረው።
ልዩ ልዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥናቶችን በማቅረብም በየጊዜው ለሚገጥሙ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲዘጋጁ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ አእንደነበርም ገልፀዋል።
በጉባኤው የክልሉ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ተነስተው ምክክር የሚደረግባቸው ሲሆን፥ የዩኒቨርሲቲዎች ልዩ ተሞክሮዎችም ይቀርባሉ።
በሙሉጌታ ደሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.