Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ከዳር ለማድረስ የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች ሁሉን አካላት ባሳተፈ መልኩ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በፕሪቶሪያው የተደረሰውን ስምምነት ከዳር ለማድረስ የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች ሁሉን አካላት ባሳተፈ መልኩ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ፥ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት እንዲተገበር ለማድረግ ሁሉም አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በተደረሰው የሰላም ስምምነት የትግራይ ህዝብ የሰላም አየር ማግኘቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ይህን በዘላቂነት ለማስቀጠል በሰላም ስምምነቱ ለተገባው ቃል ተፈጻሚነት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አያይዘውም መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በስምምነቱ የገባቸው ቃሎች ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም መንግስት በተደረሰው ስምምነት መሰረት በየብስ እና በአየር ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ ሰብአዊ ድጋፎችን እያደረሰ ነው ብለዋል።

በዚህም በአፋር አብ አላ፣ ጎንደር – ማይጸምሪ – ሽረ እና ኮምቦልቻ – ቆቦ አላማጣ መስመር ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እስከ ታኅሣሥ 5 ቀን ድረስ ከ93 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እንዲሁም ከ8 ሺህ ቶን በላይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ እና ከ833 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ መግባቱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈም በአጋር አካላት በኩል 158 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት ወደ ክልል መላኩን ጠቅሰው፥ 588 ሚሊየን ብር ለስራ ማስኬጃ መላኩንም ነው የገለጹት።

በተደረገው ሰብአዊ ድጋፍም እስከ ታህሳስ 7 ቀን ድረስ 29 አጋር አካላት ተሳትፎ አድርገዋልም ነው ያሉት።

ከሰብአዊ ድጋፍ ባሻገር የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ባለው ስራም በክልሉ 85 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍተሻና ጥገና ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የመቀሌ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን ጨምሮ 8 የኃይል ጣቢያዎች ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ ግሪድ ጋር የማገናኘት ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።

በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አገግልግሎት በቀጣዮቹ 2 ወራት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባም አንስተዋል።

ከቴሌኮም ጋር በተያያዘም 65 የቴሌኮም ጣቢያዎች ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን በማንሳት፥ በ8 ከተሞች ባንክ ማስጀመር የሚያስችል ኔትወርክ ስራ መጠናቀቁንም ነው ያስረዱት።

ከመንገድ መሰረት ልማት ጋር በተያያዘ 6 ድልድዮች ስራ ጀምረዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በአክሱም፣ አድዋ እና ሽረ ከ2 ሺህ 200 በላይ የጤና ባለሙያዎች ወደ ስራ ለመመለስ ዝግጅት ማድረጋቸውንም አመላክተዋል።

የመሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦትም በተመረጡ ቦታዎች ለዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ተጀምሯል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ከቀረበው ሰብአዊ ድጋፍ ባለፈም በአማራ ክልል 54 ወረዳዎች እንዲሁም በአፋር 21 ወረዳዎችን በሴፍቲኔት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.