Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት መጀመሩን የክልሉ ግብርና ጽኅፈት ቤት አስታወቀ።

በበጋው የመስኖ ልማት “ቀቀባ” እና “ኪንግ በርድ” የተሰኙ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን ለመዝራት ዝግጅት መጠናቀቁም ተጠቁሟል፡፡

በክልሉ ከ19 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት ዕቅድ መያዙም ተመላክቷል፡፡

የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤታማ ምርት ለመሰብሰብ አቅደናል ያሉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው፡፡

የግብርና ባለሙያው ለአርሶአደሩ  ግንዛቤ እየፈጠረ የክልሉን እቅድ ለማሳካት እየሰራ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

የውሃ አጠቃቀምን በማሳደግ ውሃ ገብ የሆኑ የክልሉ አካባቢዎችን በማልማትም እንደሀገር የተያዘውን የበጋ መስኖ ልማት እቅድ ለማሳካት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን የውሃ ፓምፕ እጥረት ለመፍታትም የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በዓለምሰገድ አሳዬ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.