Fana: At a Speed of Life!

ከአቢ ዓዲ – ዐድዋ የተዘረጋው የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና 90 በመቶ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአቢ ዓዲ – ዐድዋ የተዘረጋው የባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና 90 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ጥገና በአብዛኛው በመጠናቀቁ የዐድዋ እና አክሱም ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ በነገው ዕለት የሙከራ ሥራ እንደሚሠራ በተቋሙ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የጥገና እና ቴክኒካል ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከዐድዋ – ሽሬ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ የተዘረጋው የ66 ኪሎ ቮልት የሥርጭት መስመር በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠግኖ የተጠናቀቀ ቢሆንም ከሽሬ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ለመስጠት የሙከራ ሥራ ሲከናወን በብሬከሩ ላይ ችግር ማጋጠሙን ነው የገለጹት።

የብሬከሩን ብልሽት በመጠገን ከመስመሩ ኃይል የሚያገኙ አካባቢዎች ኃይል እንዲያገኙ እንደሚደረግ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.